ፍርድ ቤቱ በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ

72
አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀድሞ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ኡመር መሐመድ ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ፈቀደ። የተጠርጣሪ ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊሲ ለምርመራ የጠየቀውን ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ተቃውመዋል። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎች በዛሬው ውሎው በአቶ አብዲ ኡመር መሃመድ መዝገብ ስር ክስ የቀረበባቸውን ሌሎች ሶስት ግለሰቦችን ጉዳይም ተመልክቷል። ግለሰቦቹ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከ2004 ዓም ጀምሮ በሶማሌ ክልል በተፈፀመ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም ደግሞ በክልሉ ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር እንዲሁም አስገድዶ በመድፈር ወንጀል ተጠርጥረው ነው። ፖሊስ በዚሁ ወቅት ለፍርድ ቤቱ በሰጠው ማብራሪያ በሶማሌ ክልል ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የተፈፀሙት ወንጀሎች ውስብስብ ባሕሪ ያላቸና በተደራጀ መንገድ የተከናወኑ በመሆናቸው ወንጀሎቹን በማጣራት ሂደቱ ችግሮች እየገጠሙት መሆኑን አስታውቋል። በተለይም ከሐምሌ 26 እስከ 30 ቀን 2010 ዓ.ም በክልሉ በነበረው ሁክትና ብጥብጥ ላይ ተጎጂ የሆኑ ዜጎችን እግኝቶ ቃላቸውን የመቀበል ስራ ለማጠናቀቅ ጊዜ አንደሚያስፈልገው ፖሊስ አስረድቷል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ በጅምላ የተገደሉ የ200 ሰዎች አስከሬንን ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እየመረመረና ሙያዊ ትርጉም በማሰጠት የጉዳት መጠን እንዲለይ በማድረግ ላይ  መሆኑንም አመልክቷል። የተጠርጣሪ ቤተሰቦች በጎሳ በመደራጀት የምርመራ ሥራውን የማደናቀፍ ተግባር እየፈፀሙ መሆኑን የጠቀሰው ፖሊስ እነዚሁ አካላት ምስክሮችን በማባባልና ከአገር እንዲወጡ በማድረግ እንቅፋት እየፈጠሩ ነው ሲልም ፖሊስ ለችሎቱ አብራርቷል። የግራ ቀኝ ክርክሩን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ ለታሕሳስ 11 ቀን 2011 ዓም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም