ሊበን መሐመድ የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ውድድርን የመጀመሪያ ወርቅ አገኘ

68
አዲስ አበባ ህዳር 27/2011 ሊበን መሐመድ በብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አገኘ። የ2011 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር ብሔራዊ የክለቦች የቦክስ ውድድር ትናንት በድሬዳዋ ተጀምሯል። በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ከሰባት ክለቦች የተወጣጡ 80 ቦክሰኞች እየተሳተፉ ነው። ትናንት በተጀመረው ውድድር ከ91 ኪሎ ግራም በላይ የወንዶች የፍጻሜ ጨዋታ የድሬዳዋ ከነማው ሊበን መሐመድ የፌዴራል ፖሊሱን አዲሱ ሁንዴሳን በማሸነፍ የውድድሩን የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። በተመሳሳይ የወንዶች የ49፣ 52፣ 56 እና 60 ኪሎ ግራም የማጣሪያ ውድድሮች መካሄዳቸውን የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል። ዛሬ በሴቶች የ48 ኪሎ ግራም የድሬዳዋ ከነማ አገሬ እማኙ ከአዲስ አበባ ፖሊሷ ቤተልሄም ገዛኸኝ ጋር ለፍጻሜ ለማለፍ ይጋጠማሉ። የወንዶች ከ52 እስከ 91 ኪሎ ግራም ክብደት 11 የማጣሪያ ጨዋታዎችም ይካሄዳሉ። የውድድሩ ዓላማ ተተኪ ቦክሰኞችን መመልመልና ብቁ ተወዳዳሪዎች ማፍራት እንደሆነ የገለጹት አቶ ስንታየሁ በዓመቱ መጨረሻ በሞሮኮ ለሚካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን የሚወክሉ የቦክስ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ እንደሚያግዝም አስረድተዋል። ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በዓመት አራት ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ቀሪዎቹ ውድድሮች በወላይታ፣ ጅግጅጋና አዲስ አበባ ይካሄዳሉ። በአራቱ ብሔራዊ የቦክስ ውድድሮች የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ቡድኖች ውጤት ድምር የ2011 ዓ.ም ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች አጠቃላይ አሸናፊ ይሆናሉ። ትናንት በድሬዳዋ የተጀመረው የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ውድድር እስከ ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም ይቀጥላል። የ2010 ዓ.ም የብሔራዊ ቦክስ ክለቦች ውድድር አጠቃላይ አሸናፊዎች በወንዶች ፌዴራል ፖሊስ በሴቶች ደግሞ አዲስ አበባ ፖሊስ ነበሩ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም