በ"ግፍ ከመሬታቸው" የተፈናቀሉት አርሶ አደሯ የጎዳና ተዳዳሪ ሆነዋል

25

አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 የ48 ዓመቷ ወይዘሮ ሙሉ ደምሴ ከልጆቻቸው ጋር በእዚች በላስቲክ ሸራ በተሰራች መጠለያ መኖር ከጀመሩ ከስምንት ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ የሰሜን ሆቴልን ግርግዳ ታከው መኖር ከመጀመራቸው ከዓመታት በፊት የእርሻ መሬታቸውን አሳርሰው በሚያገኙት ገቢ ኑሯቸውን መርተዋል። ዘጠኝ ቤተሰባቸውን አስተዳድረዋል፤ ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ልከዋል። ዛሬ ያሁሉ ቀርቷል። በ"ደረሰባቸው በደል" የሚወዷቸውን ሁለት ልጆቻቸውን እስከ መጨረሻው አጥተዋል። ዛሬ አምስት ልጆቻቸውን ይዘው በጎዳና ተዳዳሪነት የእለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ምጽዋት ይጠይቃሉ።

ትዳር መስርተው ልጆች ወልደው በደስታ ከሚኖሩበት የትውልድ ቀያቸው ከፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሱሉልታ ወረዳ ደርባ ጉለሌ በሬሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የወጡበት ምክንያት ከአባታቸው የወረሱትን አምስት ሄክታር መሬት "በግፍ ተቀምቼ ነው" ይላሉ።

 

ነገሩ የሚጀምረው እንዲህ ነው። ባለቤታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ በኋላ የእርሻ መሬታቸውን አቶ መስፍን በረዳ ከተባለ ግለሰብ ጋር እኩል አርሰው ለመካፈል ስምምነት ያደርጋሉ።  ግለሰቡ ከወይዘሮ ሙሉ ጋር ባደረገው ስምምነት መሰረት የእኩል በማረስ ለአምስት ዓመት ይቆያል። ቀስ በቀስ ግን "መሬቱ ልውጫ" ነው በሚል እንዲያስረክቡት ያስገድዳቸዋል።

"መጀመሪያ የእናት የአባቴ መሬት ነበር። እነሱ ሲሞቱ እኔ ወረስኩኝ። ከዚያ እኩል እያረሰን መጣና በኋላ ላይ ልውጫ ነው ብሎ ካደኝ። አዙሮብኝ። በስቃይ ሁለት ልጆች ናቸው የሞቱብኝ። ከዚያ ማደሪያ አጥቼ መጥቼ እዚህ ላይ ወደኩኝ ያው አሁን ያለሁበትን ሁኔታ እያያችሁ ነው።መጨረሻ ላይ ካደኝ እንደውም ቀወስኩኝ “

ግለሰቡ ከወይዘሮ ሙሉ ያገኘው “ይሁንታ” ሳይኖር አምስት ሄክታር መሬት ሲቀማ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መፍትሄ እንዴት አልሰጡም? ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ግድ ይላል።

“እነርሱ ናቸው እንደውም ተባብረው ነው። ከሊቀ መንበሩ ጋርም ተባብረው ለእነሱ ጉቦ እየሰጣቸው ጫንጮ ላይም አስፈረደብኝ።ሲሰለቸኝ ወደኩኝ እዚህ ቀረሁ።ይህው ለምኜ ነው የምኖረው ልጆቼን ይዤ።”

የኢዜአ ሪፖርተር ይኖሩበት ወደ ነበረው ትውልድ ቀያቸው ሄዶ ሲያጣራ የወይዘሮ ሙሉ የተሟላ ሰነድ በቀበሌ ማህደር ውስጥ መኖሩን አረጋግጧል። ወይዘሮዋ የሱሉልታ ገቢዎች ባለስልጣን ኅዳር 3 ቀን 2011 ዓ.ም በቁጥር ATG AB1559/11 በተፃፈ ደብዳቤ በ2000 ዓ.ም ለአምስት ሄክታር መሬት 196 ብር ዓመታዊ ግብር መክፈላቸውን ያሳያል።

የአቶ መስፍን ግን የለም። "ልዋጭ አድርገን ነው" የሚለውንም የሚያረጋግጥ ማስረጃም አልተገኘም።

የወይዘሮ ሙሉ ልጆች ባለትዳሯ ወርቄ ዳባ፤ ግለሰቡ የእናታቸውን መሬት በእኩል በማረስ ለማካፈል ሲሰራ እንደነበር ያውቃሉ። ድንገት ግን "ልውጫ ነው ብሎ መሬቱን ቀማት" ይላሉ።

“እርሷ በቃ ድህነት ላይ ወደቀች። እንጨት፣ ኩበት እየለቀመች ነው ልጆቿን እያሳደገች የኖረችው። እኔም ልጅ ሆኜ አብሪያት ነበር እንጨት ለቅሜ የምኖረው ከዚያም ከፍ ስንል የምንለብሰው ስናጣ ረሀብ ሲያሰቃየን ተሰደድን። ሁለት ሴት እህቶቼ በረሀብ ሞተዋል፤ በህይወት ያለነው ደግሞ ተበታተንን። እናታችንም እዚህ ሸራ ወጥራ መኖር ከጀመረች ረጅም ጊዜ ሆናት።”

የኢዜአ ሪፖርተር ወይዘሮ ሙሉ ይኖሩበት ወደ ነበረው አካባቢ በተንቀሳቀሰበት ወቅት ያነጋገራቸው ጎረቤቶች "መሬቷን በግፍ ተቀምታለች፤ የሚሰማት ሰው፣ ፍትህ የሚሰጣት አካል አጣለች" በማለት ይገልጻሉ።

“ስትኖር እኩል እየሰጠች ነበር። እርሱ እኩል አርሳለሁ ብሎ ወሰደው። ሲወስድ ምንም ሳይሰጥ ከለከላት። ሲከለክላት ፍርድ ቤትም ቀርባ የእርሷ ፋይል አይወጣም። ሁል ጊዜ ያፍናታል፤ ገንዘብ የላትም፤ ሳንቲም የላትም፤ ቤተሰቦቿንም ስቃይ ያሳያል እሷም ልጆቿን ይዛ የሄደችበትን እስካሁን አናውቅም ነበር።” ያሉት አቶ ተሾመ ደቤ ናቸው፡፡

ወይዘሮ አበቤ ማሞ በበኩላቸው በአካባቢው ለ40 ዓመት እንደኖሩ ገልፀው “የሙሉን 5 ሄክታር መሬት የወሰደው መስፍን በረዳ ነው።እርሷ ደሃ ናት ልጆቿ ሞተውባት ሰው ነው የቀበረላት። መሬት እያላት ከተማ ሄዳ እየለመነች ነው” ብለዋል፡፡

ከወይዘሮ ሙሉ "በእኩል በማረስ ሰበብ መሬቱን ቀምተዋል"የተባሉትን አቶ መስፍን በረዳ " በስምምነት መሬት ተለዋውጠን ነው" ይላሉ።

 “ከወይዘሮ ሙሉ ደምሴ ጋር በ85 ዓ.ም በውል ተለዋውጠናል።መሬት በመሬት ነው የተለዋወጥነው። በተለዋወጥነው መሰረት እኔ ይዤ ቆይቻለው። በ2004 ለቀበሌ ገበሬ ማህበር አመለከተች። ባመለከተችው መሰረት በኦሮሚያ መመሪያ መሰረት ሽማግሌ ቆጠርን፤ ሽማግሌ ቆጥረን ሽማግሌው የራሱ የሆነ ቃለ ጉባኤ ይዞ ለቀበሌ አቀረበ ቀበሌው ደግሞ ለፍርድ ቤት አስተላለፈ። ፍርድ ቤት ግራና ቀኝ በማከራከር ውሳኔ ሰጠ። ውሳኔ ከሰጠ በኋላ በኔ ስር ሆነ ከዚያ በፊትም እኔ በጉልበት አልያዝኩም በውል ነው የያዝኩት” አቶ መስፍን እንዳሉት

አቶ መስፍን የአምስት ሄክታር መሬቱ የራሳቸው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ሰነድና ስለመለዋወጣቸው የሚያሳይ ውል እንዲያቀርቡ ተጠይቀው "ለሌላ ጉዳይ ጠበቃዬ ዘንድ ነው" በሚል ሰበብ ሊያሳዩን አልቻሉም። ወይዘሮ ሙሉ መሬት ቢቀያየሩ አሁን ለወደቁበት ችግር ይጋለጣሉን? ለሚለው ጥያቄ ምላሽም አላገኘንም።

ቀደም ብሎ መሬቱን አቶ መስፍን በያዙበት ወቅት ከ1984 ዓ.ም እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ የቀበሌ ገበሬ ማህበሩን በጸሀፊነት ያገለግሉ የነበሩት አቶ ጌታቸው ጉዳ እንደሚሉት መስፍን "መሬቱን ልማት ልስራበት" ብሎ ወስዷል።

“ የመሬቱ ጉዳይ መጀመሪያ የሙሉ ደምሴ መሬት ነው ይሄን አውቃለሁ። መስፍን መሬቱን ልማት ልስራበት ብሎ ከወረዳ ደብዳቤ አጽፎ መጣ ወደ እኛ ቀበሌ ሲያመጣም በፍቃዳችሁ ነው ወይ ብለን ጠየቅን አዎ ፈቅደን ነው ብለዋል።”

አቶ መሰፍን እና የቀድሞ የቀበሌ ገበሬ ማህበሩ ፀሐፊ የነበሩት አቶ ጌታቸው ይሄንን ይበሉ እንጂ የኢዜአ ሪፖርተር የአካባቢው ሽማግሌዎችና የመስተዳድር አካላት ጠይቆ እንዳረጋገጠው አቶ መስፍን የሰጡትም ልዋጭ መሬት አልነበራቸውም። ስለስምምነቱም የሚያውቁት ነገር የለም።

በሱሉልታ ወረዳ የደርባ ጉለሌ በሬሳ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሊቀ መንበር አቶ ደጀኑ ተሰፋዬ ወይዘሮ ሙሉ ህጋዊ የቦታው ባለንብረት እና ግብር ከፋይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

"እርሷ በቅድሚያ ግብር ከፋይ መሆኗን አውቃለሁ። ሁለቱ ይተዋወቁ እንጂ እኛ በልውጫም በክራይም የምናውቅው ነገር የለም። ሙሉ ባለይዞታው ናት ግብር ከፋይ ናት እርግጠኛ ነኝ። በእኛ ደረጃ ያልተፈታበት ምክንያት ምስጥሩን ስለማናውቅ ነው እርሱ በልውጫ ነው ያዝኩት ይላል። ግማሹን በኮንትራት ይላል ውሉን አቅርቡ አልን። የቀረበልን ነገር የለም።

 

እንደሊቀ መንበሩ ገለጻ ከሆነ አቶ መስፍን በ2009 ዓ.ም ከፍርድ ቤት ሰነድ ለቀበሌው ሰጥተዋል። በወቅቱ ፍርድ እንዴት እንደተሰጠ ግን የሚያውቁት ነገር የለም

ይህን የእርሳቸው ሀሳብ የሚያጠናክርና በፍርድ ሂደቱ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ሀሳብ ያጋሩን በወቅቱ ለከሳሾች አቤቱታ ይጽፉ የነበሩ አቶ አሰፋ ነጋሳ ናቸው።

“ወይዘሮ ሙሉ ደምሴ  የምትባል አንዲት ሴት መታ እኔ ጋራ ክስ ጻፍልኝ ብላኝ በዛ ወቅት ላይ ክስ ጽፌላት ነበር። ክሷንም በኦፊሰር ታይቶ ለፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላ የፍርድ ቤቱ ሰውዬ እኔን በግል በመጥራት ይሄንን ክስ አቋርጠው ወይንም ደግሞ ይዘቱን ቀይር ብሎ ማስፈራሪያ ያደርግብኝ ነበር በሚጠይቀኝም ወቅት አልቀይርም በማለቴ ለሶስት ቀን ያህል ታስሬያለሁ።”

የሱሉልታ ወረዳ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛው ታደሰ ሀሳባቸውን አጋርተውናል።

 ልውጫ መኖር አለመኖሩን ቼክ ለማድረግ ነበር አኛ አካሄዳችን። በዛን ሰዓት ግን ፍቃደኛ አልነበረም ሰውየው። ፍርድ ቤት አልፈረደም ትክክለኛ አይደለም የማለት ስልጣን የለንም በሚፈርደው ግራ እና ቀኝ ምስክር አጣርቶ ሊፈርድ ይችላል። ያንን ልንሰርዝ አይደለም የተቀየረው ቅያሬ መሬት የቱ ጋር ነው እሱን ማሳየት ትችላለህ ወይ ብለን ስንጠይቅ የነበረው ያንን እኔ ከህግ በላይ አትሂዱብኝ በህግ ነው ያስወሰንኩት በህግ ነው ያገኘሁት የሚል መልስ ነው የመለሰልን።”

የሱሉልታ ወረዳ የመሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ጽህፈት ቤት የፀረ ሙስና የሥራ ሂደት ወይዘሮ ሮሚታ ለገሰ በወረዳው መሬታቸውን በተመሳሳይ መልኩ የተቀሙ በርካታ አርሶ አደሮች መኖራቸውን ይናገራሉ።

የሱሉልታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሀይለሚካኤል አበራ በበኩላቸው የወረዳ አስተዳደሩ ወይዘሮ ሙሉ የደረሰባቸውን በደል አጣርቶ መፍትሄ እንደሚሰጥ ነው ያረጋገጡት።

 “ጉዳዩ በእርግጥ ልብ የሚነካ ነው ይሄንን ችግር ወደፊት ምን ማድረግ አለብን የሚለውን መፍትሄ ለመስጠት አሁን የመሬት አስተዳደሩ እየሄደበት ያለውን ሁኔታ አጠናክረን ወደ ፊት ችግሩን ለመፍታት ከእነሱ ጋር ሆነን እውነታው እና ሀቁ ይሄ ከሆነ እኛም እኝህን ግለሰብ ለመርዳት ወደ ኋላ እንደማንል ለማንሳት ነው። እነዚህ እጃቸው ያለባቸውን ሰዎች አረጋግጠን ወደ ህግ እንዲቀርቡ የምናደርግበትን ሁኔታ እናመቻቻለን።”

የኢዜአ ሪፖርተር ተዘዋውሮ ማስረጃዎችንም ተመልክቶ እንደታዘበው ለወይዘሮ ሙሉ በልዋጭ የተሰጠ መሬት የለም። ወሰዱ የተባሉት ግለሰብም ያቀረቡት ማስረጃ የለም። በፍርድ ቤት ቢሆንም መሬቱን እንዲይዙት የተወሰነው መሬቱ ለዓመታት እርሳቸው ጋር ስለቆየ በ"ይርጋ በሚል" እንደተወሰነላቸው የሚያሳይ መረጃ ከሱሉልታ ወረዳ ፍርድ ቤት ለማግኘት ቢቻልም እንዴትና በምን መንገድ እንደሆነ የሚያብራራ ማስረጃ የለም። ይህም ሆኖ ግለሰቡ "መሬት ተለዋውጠው" መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።

 

https://www.youtube.com/watch?v=KnKP53amvYs&t=7s

በ”ግፍ ከመሬታቸው” ተፈናቅለው የጎዳና ተዳዳሪ የሆኑት እናት አርሶ አደር
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም