ቀጥታ፡

አዲስ አበባ የብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ታዳሚ እንግዶቿን መቀበል ጀምራለች

አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 የአዲስ አበባ ከተማ የብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክብረ በዓል ቀንን ለመታደም ከመላው አገሪቱ የሚመጡ እንግዶችን መቀበል ጀምራለች። ክብረ በዓሉ ሰላማዊና የተሰካ ሆኖ ይጠናቀቅ ዘንድ በከተማው ምክትል ከንቲባ  የሚመራ የፀጥታ ግብረ ኃይል ተሰይሞ ወደ ሥራ መግባቱም ተገልጿል። ከሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የተወከሉ ከ2 ሺህ የሚልቁ እንግዶች በዓሉን ለመታደም ወደመዲናዋ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። በከተማ አስተዳደሩ የፕሬስ ሴክሬታሪ ኃላፊ ፌቨን ተሾመ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የከተማ አስተዳደሩ ቀኑን በድምቀት ለማክበር የሚያስችለውን ዝግጅት አጠናቆ እንግዶችን መቀበል ጀምሯል። ማረፊያ ሆቴሎችን ጨምሮ እንግዶችን ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች በሙሉ መከናወናቸውን ነው ወይዘሪት ፌቨን የገለፁት። ዋናው ክብረ በዓል የፊታችን ቅዳሜ ህዳር 29 ቀን 2011 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ የሚከበር ሲሆን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን ከቀኑ ጋር የተያያዙ ልዩ ልዩ ሁነቶች እስከ በዓሉ ፍጻሜ ድረስ በመከናወን ላይ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ የተካሄደውና ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ከ10 ሺህ በላይ ህጻናት የተሳተፉበት የባህል ፌስቲቫል   ይገኝበታል። ከዚህም ሌላ ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ፤ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ያመጡ ከ6ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎች ጉብኝትም ሌላው ክንዋኔ ነው። ነገ ሐሙስ ህዳር 27 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ "ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ " በሚል መሪ ቃል በመስቀል አደባባይ 10 ሺህ ታዳሚያን የሚሳተፉበት የቡና ጠጡ ስነ ሥርዓት ይከናወናል። በዚሁ እለት ምሽት "ህብር ኢትዮጵያ" የተሰኘና  በሺህዎች የሚቆጠሩ እንግዶች የሚታደሙት የሙዚቃ ድግስ በጊዮን ሆቴል ይከናወናል ተሏል። በዓሉን በማስመልከት የሚካሄደው ልዩ ልዩ መርሃ ግብር በዓይነቱ ልዩ በመሆኑ በዓለም አቀፍ ድንቃድንቅ መዝገብ ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግም ወይዘሪት ፌቨን ጠቁመዋል። ከበዓሉ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑት ሁነቶች በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚካሄዱ ውይይቶችንም ያካትታል። መላው የአዲሰ አበባ ከተማ ነዋሪ በተለመደ የእንግዳ ተቀባይ ባህሉ እንግዶቹን እንዲያስተናግድ ወይዘሪት ፌቨን ጥሪ አቅርበዋል። በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የሚመራ የፀጥታ ግብረ ኃይል ተሰይሞ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም