ወጣቱ ከመጠራጠርና ከጥላቻ ፖለቲካ ተላቆ በሀገር ግንባታ ላይ ሊያተኩር ይገባል....የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ከመጠራጠርና ከጥላቻ ፖለቲካ ተላቆ በሀገር ግንባታ ላይ ሊያተኩር ይገባል....የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች
ባህር ዳር ህዳር 26/2011 የኢትዮጵያ የቀደመ ክብርና አንድነት ተጠብቆ እንዲቆይ ወጣቱ እርስ በርስ ከመጠራጠርና ከጥላቻ ፖለቲካ ተላቆ በሀገር ግንባታ ላይ ሊያተኩር ይገባል ሲሉ በባህር ዳር የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ተናገሩ። በክልሉ ዕስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት አዘጋጅነት የተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ተጠናቋል። ከኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መካከል ሀጂ ሙስጠፋ ሰኢድ ለኢዜአ እንደገለጹት ወጣቱ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከመነዳት ወጥቶ ስለሀገራዊ አንድነትና ዕድገት አተኩሮ ሊሰራ ይገባል። የጥፋት ኃይሎች የግል የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሲሉ ከ40 ዓመት በፊት የተፈፀመን ጉዳይ በማንሳት ህዝቡን እርስ በርስ ለማጋጨትና ሀገሪቱ ሰላሟ እንዳይረጋገጥ ሌት ተቀን እየሰሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል። "በሀገሪቱ ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው የኖሩ ህዝቦችንና ሃይማኖቶችን በማጋጨት ሰላም እንዳይኖር ከሚሰሩ ኃይሎች ወጣቱ ራሱን በማራቅ ለሀገሩ ሰላም ዘብ ሊቆም ይገባል" ብለዋል። በተለይ አሁን እየተስተዋለ ካለው የእርስ በርስ መናቆርና የጥላቻ ፖለቲካ ወጣቱ መውጣት እንዳለበት ጠቁመው የአገሪቱ ሰላም በዘላቂነት እንዲረጋገጥና የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል ወጣቱን ስለሰላም ለማስተማር መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል። ሸህ ቃሲም መሀመድ በበኩላቸው "የሀገሩቱን አንድነትና የቀደመ ክብር ጠብቆ ለማቆየት የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነው ወጣት ከዘረኝነትና ጎጠኝነት አስተሳሰብ መላቀቅና ስለሀገር አንድነት ቆም ብሎ ማሰብ አለበት" ብለዋል። "የኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና የሚታሰበው ሰላሟን መሰረት በማድረግ ነው" ያሉት ሼህ ቃሲም የሃይማኖት ሊቃውንቱ ስለሰላም ጠቀሜታ ለወጣቱ በየቤተ ዕምነቱ ተግተው እንዲያስተምሩ አስገንዝበዋል። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ዕድል ያገኙ ተማሪዎችም ራሳቸውን ከግጭት በማራቅ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ዕድገት ሊያስቡና ሊጨነቁ እንደሚገባ አመልክተዋል። መንግስት ህዝቡን ለግጭትና ለብጥብጥ የሚያነሳሱ የልማትና የመልክም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለይቶ በመፍታት ለሰላም መጠበቅ መስራት እንዳለበት የገለጹት ደግሞ ሸህ ኑሩ እስሌማን ናቸው። "ወጣቱን ስለሰላም አስፈላጊነት በማስተማር የሰላሙ ባለቤት ራሱ እንዲሆንና እንዲጠብቀውም የሃይማኖት አባቶች ትልቁን ድርሻ ወስደን ልናስተምር ይገባል" ሲሉም ተናግረዋል። ሼህ ኢብራሂም ሁሴን በበኩላቸው "የወረረንን ዘረኝነት ነቅለን ለማጽዳት ወላጅ በቤት ውስጥ፣ የሃይማኖት አባቶች ደግሞ በየቤተ ዕምነቱ ስሰላም፣ ስለአንድነትና አብሮነት አብዝተን ልናስተምር ይገባል" ብለዋል። ወጣቱ ሃይማኖትንና ዘርን መሰረት አድርጎ ወደግጭት ከሚያስገቡ ነገሮች ራሱን እንዲያርቅ በኃላፊነት ለመስራት መዘጋጀታቸውን የሃይማኖት አባቶቹ ገልጸዋል። ለአንድ ቀን በተዘጋጀው የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የምክር ቤት አባላትና ተጋባዥ እንግዶች መሳተፋቸው ታውቋል።