ከ246 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተከናወነው የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ - ኢዜአ አማርኛ
ከ246 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተከናወነው የኤሌክትሪክ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ
ጎንደር ህዳር 26/2011 የጎንደር ከተማና አካባቢውን የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከ246 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሲካሄድ የቆው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ተገለጸ፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል የጎንደር ፕሮጀክት ሳይት ማናጀር አቶ ዳዊት ገብረእግዚአብሔር ለኢዜአ እንደተናገሩት በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ነባር የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም ከ40 ሜጋዋት ወደ 166 ሜጋዋት ማሳደግ ተችሏል፡፡ በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ 15ሺህ ቮልት የሚሸከሙ የ2 ትራንስፎርመሮች ተከላ ሥራን ጨምሮ ነባሩን የኤሌትሪክ ማከፋፈያ አቅም የማሳደግ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ላለፈው አንድ ዓመት ሲከናወን መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ዳዊት ባለፈው ወር ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት እንዲገባ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ "የፕሮጀክቱ መጠናቀቅ በጎንደር ከተማ ይስተዋል የነበረውን የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር ሙሉ በሙሉ መፍታት አስችሏል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡ ከጎንደር ከተማ በተጨማሪ የዳባት፣ የደባርቅ፣ የትክል ድንጋይና የሳንጃ ከተሞችን እንዲሁም የጭልጋና የቆላድባ ከተሞችንም የኤሌትሪክ ኃይል ችግር እየፈታ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡ የጎንደር ቁጥር 3 አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ መስፍን ገብረስላሴ በበኩላቸው "በማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በከተማው ማታ ማታ በሚከሰተው የኃይል ፍላጎት ጫና ምክንያት ያጋጥም የነበረውን የመብራት መቆራረጥ ማስቀረት ተችሏል" ሲሉም ገልጸዋል፡፡ በአዘዞ አካባቢም በአራት ኢንዱስትሪ መንደሮች ይስተዋል የነበረውን የኃይል አቅርቦት ችግር መፍታት ከመቻሉም በላይ የኤሌትሪክ ኃይል ለማግኘት ወረፋ ይጠባበቁ የነበሩ ባለሀብቶችን ማስተናገድ እንደተቻለም አስረድተዋል፡፡ አቶ መስፍን እንዳሉት የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የጎንደር ከተማና አካባቢውን የኃይል አቅርቦት ፍላጎትና ጥያቄዎች ለቀጣዮቹ 10 ዓመታት ለማስተናገድ የሚያስችል ነው፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ ወደአገልግሎት መግባትን ተከትሎም በከተማው አዳዲስ የኃይል ተሸካሚ የኤሌትሪክ መስመሮችን ዝርጋታ ሥራ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት በመካሄድ ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡ በጎንደር ከተማ የሚገኘው ጸሐይ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ዩንየን ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አቤ ዩኒየኑ ላቋቋመው የሰሊጥ ማበጠሪያና የዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ የጠቀየውን 450 ኪሎ ዋት ተጨማሪ የኤሌትሪክ ኃይል በቅርቡ ማግኘቱን ተናግረዋል፡፡ ዞብል የቤት ክዳን ቆርቆሮ ፋብሪካ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ደሳለኝ በበኩላቸው ፋብሪካው ለሚያስፈልገው የኤሌትሪክ ኃይል አንድ ትራንስፎርመር በመግዛት በቅርቡ የኃይል ተጠቃሚ መሆን እንደቻለ ገልጸዋል፡፡ በኢንዱስትሪ መንደሩ የሚታየውን ተደጋጋሚ የኤሌትሪክ ኃይል መቋረጥ ለማስቀረት የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ኃይል እራሱን የቻለ መስመር ለኢንዱስትሪ መንደሩ በመዘርጋት የባለሀብቱን ቅሬታ በዘላቂነት እንዲፈታም አቶ ብርሃኑ ጠይቀዋል፡፡