በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሎጂስቲክ ስርዓትን መፍጠር የሚያስችል ብሄራዊ ካውንስል ሊቋቋም ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሎጂስቲክ ስርዓትን መፍጠር የሚያስችል ብሄራዊ ካውንስል ሊቋቋም ነው
አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 የኢትዮጵያን የሎጀስቲክ ስርዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ ብሔራዊ ካውንስል የማቋቋምና ደንቦችን የማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን የኢትዮጵያ ማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን አስታወቀ። የኢትዮጵያ የሎጅስቲክ አሰራር ቀልጣፋና ውጤታማ አለመሆኑ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ ማድረጉ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። የመሰረተ ልማት፣ የፖሊሲ ጉዳዮች፣ የሎጂስቲክ ሰርቪስ አቅራቢዎች ብቃት እንዲሁም የንግድና የፋይናንስ አሰራሩ ደግሞ በዋናነት የሚነሱ የዘርፉ ማነቆዎች ናቸው። ባለስልጣኑ ይህን ችግር ይፈታል የተባለለትን አዲስ የሎጅስቲክ ስትራቴጂ ያዘጋጀ ሲሆን፤ ሰነዱም በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ አግኝቷል። የስትራቴጂክ ሰነዱ ገቢራዊነት በተለይ የእቃዎች የወደብ ላይ ቆይታና የመርከቦች ባህር ላይ ቆይታ ችግርን በመፍታት ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ተገልጿል። የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያለው የሎጂስቲክ ስርዓት ወደ አገር ውስጥ ለሚገቡና ወደ ውጭ ለሚላኩ ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነት ላይ ማነቆ ሆኖ ቆይቷል። የእቃዎች የወደብ ላይ ቆይታ፣ የመርከቦች ባህር ላይ ቆይታ፣ የትራንዚት ጊዜ መራዘም እንዲሁም የወጪው ከፍተኛ መሆን አገልግሎቱ በተለይም ከተጠቃሚው አንጻር በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዳይሆን ማድረጉ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል። ይህም የሎጂስቲክ ስትራቴጂው በአገሪቷ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ተጽእኖ እንዳይፈጠር ለማድረግና ማነቆዎችን ለመፍታት የመፍትሄ ፓኬጅ በመሆን የሎጂስቲክ ስርዓቱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚያስችል መሆኑንም ጠቁመዋል። ለዚህም አሰራር እንዲሆን ብሔራዊ ካውንስል የማቋቋም፣ ደንቦችን የማዘጋጀት፣ በወደቦች ላይ የሚኖረውን የእቃዎች ቆይታን የመቀነስና ቀልጣፋ የትራንስፖርት ሲስተም የመዘርጋት ስራዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚሰሩ ስራዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል። ለአብነትም በዓመት አራት ሚሊዮን ቶን የብትን ጭነት ወደ አገር ውስጥ ይገባል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህም 90 በመቶው የመንግሥት ጭነት መሆኑንና ከግዥ ጀምሮ እስከ ማቅርብ ድረስ በሚገባ ስለማይቀናጅ መርከቦች ወደብ ላይ ይቆያሉ ብለዋል። እነዚህን አሰራሮች በማቀናጀት የኢትዮጵያን የብትን ጭነት ያለ መርከብ ቆይታ በአጭር ጊዜ የማንሳት ውጤታማ ሥራ ለመሥራት አዲሱ ስትራቴጂክ ሰነድ እንደሚያግዝ ገልጸዋል። ይህም የውጭ ምንዛሬን ከማዳንና ከማሳደግ ብሎም አጠቃላይ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማበርከት አኳያ የላቀ ሚና እንዳለውም ተገልጿል።