በማዕከላዊ ጎንደር ቆላድባ ከተማ የተነሳ ግጭት የህይወትና የንብረት ውድመት አስከተለ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ቆላድባ ከተማ የተነሳ ግጭት የህይወትና የንብረት ውድመት አስከተለ
ጎንደር ህዳር 26/2011 በማእከላዊ ጎንደር ቆላድባ ከተማ ዛሬ ቀትር ላይ በተነሳ ግጭት የሁለት ሰዎች ህይወት ሲጠፋ ሌሎች ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን የምስራቅ ደንቢያ ወረዳ አስተዳደርና ጸጥታ ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ወንድዬ ወልደማርያም ለኢዜአ እንደገለጹት ግጭቱን ያስነሱት በከተማው የሚገኙ ወጣቶች በቁጣ ስሜት ተነሳስተው ነው፡፡ በግጭቱ ሁለት መኖሪያ ቤቶችም በቃጠሎ መውደማቸውን ሃላፈው ተናግረዋል፡፡ የወረዳው አስተዳደር የፖሊስ አባላትና የጸጥታ መዋቅሩ የተፈጠረውን ግጭት ለማስቆምና ከተማውን ወደ መረጋጋት ለመመለስ በጋራ እየተረባረቡ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ በከተማው ታዋቂነት ያላቸው ወጣቶች የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም ወደ ግጭት የገቡ ወጣቶችን በማረጋጋት የማወያየት ስራ እያካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ጭልጋ አካባቢ ከትናት በስቲያ በተፈጠረ ግጭት የአንድ ሰው ህይወት ሲያልፍ ሌሎች ስምንት ሰዎች መቁሰላቸውንና በንብረት ላይም ጉዳት መድረሱ መዘገቡ ይታወሳል፡፡