ቀጥታ፡

የቁጠባና ብድር ሕብረት ሥራ ማህበራት የሀገሪቱን ፋይናንስ እያጎለበቱ ነው--- የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች

መቀሌ ህዳር 26/2011 የቁጠባና ብድር ሕብረት ሥራ ማህበራት የህብረተሰቡ የቁጠባ ባህልና የሀገሪቱ የፋይናንስ አቅም እንዲጎለብት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጹ። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት በትግራይ ክልል የሚገኙ የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት ለህብረተሰቡ ተደራሽ ከመሆን ባለፈ የሀገሪቱ የፋይናንስ አቅም ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲሸጋገር አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አቶ አማረ ብርሃነ እንደገለጹት ህብረተሰቡ በማህበራቱ በኩል የሚቆጥበው ገንዘብ ባለሀብቶች ከባንክ ተበድረው ለልማት እንዲጠቀሙበት በማድረጉ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲኖር አድርጓል፡፡ የባንክ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሃብቶም ግደይ በበኩላቸው ከያንዳንዱ ግለሰብ የሚቆጠበው ገንዘብ በሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ የጎላ አስተዋፅኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦች በባንክ የሚያስቀምጡት ገንዘብ ለአገር ከሚኖረው ፋይዳ ባለፈ የቁጠባ ባህላቸውን በማሳደግ ለራሳቸው የሚሰጠው ጥቅም የላቀ መሆኑን ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ በመቀሌ ከተማ የሚገኘው የሚዛን ቁጠባና ብድር ኃላፊነቱ የተወሰነ ህብረት ሥራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ መብራህቱ ተአምራት ነገ ወደተሻለ ስኬት ለመድረስ ዛሬን መቆጠብ አስፈላጊ መሆኑን መክረዋል፡፡ በትግራይ ክልል 555 ሺህ 342 አባላት የሏቸው 944 የቁጠባና ብድር ህብረት ሥራ ማህበራት መኖራቸውን የገለጹት ደግሞ በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ የህብረት ሥራ ማህበራት ማስፋፊያ የፋይናንስ አመራር ዳይሬክተር አቶ ፍስሃ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡ በማህበራቱ 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር መቆጠባቸውን ያስረዱት ዳይሬክተሩ ይህን ከፍተኛ መዋዕለንዋይ ለልማት በማዋል ለሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት የድርሻውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ በመደረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ማህበራቱ ባንኮች በማይደርሱባቸው አካባቢዎች በመድረስ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን ይበልጥ ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ አታክልቲ ኪሮስ በቅርቡ ባካሄዱት ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ የመንግስትና የግል ባንኮች ከ133 ሺህ የማይበልጡ ተበዳሪዎች መኖራቸውን እንዳረጋገጡ  አስታውቀዋል። የባንኮች የተበዳሪዎች መጠን ከ100 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ካላት አገር አንፃር ሲታይ በእጅጉ ዝቅተኛ ነው ብለዋል ባለሙያው። የአነስተኛ ቁጠባና ብድር ተቋማትና የህብረት ሥራ ማህበራት ከህብረተሰቡ ገንዘብ በመሰብሰብ ለባንኮች እያደረጉት ያለው ድጋፍ ቀላል አለመሆኑን የተናገሩት ባለሙያው ተቋማቱን በአቅምና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መደገፍ እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ከኢትዮጵያ አነስተኛ የፋይናስ አቅራቢ ተቋማት ማህበር የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት 38 አነስተኛ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ተቋማት አምስት ሚሊዮን ተበዳሪ አላቸው። ተቋማቱ 50 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ በማበደር በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውም ተመልክቷል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም