ለስደተኞች የቴክኒክና ሙያ አጭር የሥልጠና መርኃ ግብር ተጀመረ

64
አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 ከጀርመን መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው ለኢትዮጵያውያንና ለስደተኞች ሁሉን አቀፍ የቴክኒክና ሙያ የአጭር የሥልጠና መርኃ ግብር ተጀመረ። መርኃ ግብሩ የሚከናወነው በንፋስ ስልክ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንደሆነ ተጠቁሟል። በመርኃ ግብሩ ከኢትዮጵያውያን፣ ከኤርትራ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን፣ ከየመንና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የመጡ ስደተኞችን ተጠቃሚ ያደርጋል። በዚህም መሰረት በመጀመሪያው ምዕራፍ 75 ስደተኞችና 65 ኢትዮጵያውያኖች በስድስት ዘርፎች ላይ ለአምስት ወር ሥልጠናውን እንደሚያገኙ ተገልጿል። ዘርፎቹ አውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ፣ ብየዳ፣ ልብስ ስፌት፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የምግብ ዝግጅትና የዳቦ ጋገራ መሆናቸው ታውቋል። መርኃ ግብሩ ስደተኞች በአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት የሚቀርበው የሙያ ሥልጠና እድል ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል ተብሏል። ይህም ኢትዮጵያ ተቀብላ ያጸደቀችውን ሁሉን አቀፍ የስደተኞች ምላሽ ማዕቀፍን በማጠናከር ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑም ተገልጿል። ሰልጣኞቹ በ ጂ አይ አይ ዜድና ከሌሎች የዘርፉ ተቋማት በተውጣጡ ባለሙያዎች በተዘጋጀው አዲስ ሁሉን አቀፍ ሥርዓተ-ትምህርት ይታገዛሉ ተብሏል። ይህም ሥርዓተ ትምህርቱ መሰል የሥልጠና ተቋማት ኢንዱስትሪው በሚፈልገው መሰረት የሥልጠና መርኃ ግብራቸውን ለመቅረጽ እንደሚረዳቸው ተጠቁሟል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከ900 ሺ በላይ ስደተኞች ተጠልለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም