በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በቁጥጥር ስር ዋለ - ኢዜአ አማርኛ
በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ሊወጣ የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በቁጥጥር ስር ዋለ
አዲስ አበባ ህዳር 26/2011 በህገ ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል ከአገር ሊወጣ የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ። የሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ይርጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ከአዲስ አበባ ወደ ቻይና በሚጓዝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ በተደረገ ፍተሻ 6 ሺህ 170 ፓውንድ፣ 33 ሺህ 175 ዩሮ እና ከ1 ሚሊዮን 364 ሺህ ብር በላይ በቁጥጥር ስር ውሏል። ገንዘቡ በቁጥጥር ስር የዋለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኛ የሆነ ግለሰብ ያለ መፈተሽ መብቱን ተጠቅሞ ወደ ቻይና ለምትጓዝ መንገደኛ ለማቀበል ባደረገው ሙከራ መሆኑን ገልጸዋል። እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፤ የአየር መንገዱ ሰራተኛ ወዲያው በቁጥጥር ስር ሲውል ወደ ቻይና የምትጓዘው መንገደኛ ደግሞ አውሮፕላኑ ከ3 ሰአታት በረራ በኋላ ተመልሶ እንዲያርፍ በማድረግ በቁጥጥር ስር ለማዋል ተችሏል። የፌዴራል ፓሊስ ጉዳዩን እያጣራ መሆኑንም አክለዋል።