ቀጥታ፡

የሐረር ህዝብ በፍቅር የመኖር ባህሉን በማጎልበት በሀገር ሰላም ግንባታ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ

ሀረር  ህዳር 26/2011 የሐረር ህዝብ የሚታወቅበትን ተቻችሎና ተከባብሮ በፍቅር የመኖር ባህል በማጎልበት በአገር ሰላም ግንባታ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሴት የሰላም አምባሳደሮች ጥሪ አቀረቡ፡፡ የኢትዮጵያ ሴት የሰላም አምባሳደሮች ትላንት በሐረር ከተማ ተገኝተው ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተወያይተዋል፡፡ ኦሮሚያ ክልልን ወክለው የተገኙት ወይዘሮ አልፍያ ሃጂ በሐረሪ ክልል አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶች በዜጎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳደሩ መሆናቸውን ተናግረዋል ። "የሐረሪ ክልል ህዝብ አንዱ ከሌላው የተዋለደና የተዛመደ ነው" ያሉት ወይዘሮ አልፍያ ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ በፍቅር የኖረ ህዝብ መሆኑንም አመልክተዋል። ህዝቡ የሚታወቅበትን በፍቅር አብሮ የመኖር ባህል በማጎልበትና ግጭቶችን በማስቀረት በሀገር ሰላም ግንባታ ውስጥ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። "የክልሉ መንግስትም በክልሉ የመልካም አስተዳደርና የፍትህ መጓደል ችግሮችን መፍታት ይኖርበታል" ብለዋል፡፡ "እኛ እናቶች ከምንም ነገር በላይ ሰላም ያስፈልገናል" ያሉት ደግሞ የደቡብ ክልልን የወከሉት ወይዘሮ ትዕግስት ትግሮ ናቸው ። ወይዘሮ ትዕግስት እንዳሉት የክልሉ ነዋሪ ለሰላም በመቆም ተምሳሌትነቱን በተግባር ማሳየት ይኖርበታል፡፡ "ካለእናት የተወለደ የለምና እናት በግጭቶች ሳቢያ ጉዳትና እንግልት ሊደርስባት አይገባም " ያሉት ወይዘሮ ትዕግስት እያንዳንዱ የክልሉ ነዋሪ ከፍቅር፣ መቻቻልና አንድነት በተጨማሪ ስለ እናቱ፣ ሚስቱና እህቱ  ሊዘምር እንደሚገባ መክረዋል፡፡ "አመራሩም በሰላምና መቻቻል ለማጎልበት እስከ ወረዳና ቀበሌ ወርዶ መስራት ይጠበቅበታል" ብለዋል፡፡ ትግራይን በመወከል የተገኙት ወይዘሮ ጃኖ ንጉሴ በበኩላቸው ሐረር የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተቻችለው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን ነው የገለጹት።   በወጣቶች የተተካው የክልሉ አዲስ አመራር ወጣቱን ቀርቦ ማወያየትና ችግሮችን አድምጦ መፍታት እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል ።   አስተዳደሩ ከመንግስት፣ ከወጣቱ፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር በመሆን የክልሉን ሰላምና ልማት ማረጋገጥ እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል።   የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ከሴት የሰላም አምባሳደሮቹ የተላለፉ ምክሮችና አስተያየቶች በግብአትነት በመውሰድ ለሥራቸው እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል ።   "የሐረር ከተማ ለዘመናት የቆየ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር እሴት ባለቤት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት አልፎ አልፎ የሰላም መደፍረስ  እየታየበት ነው" ብለዋል ፡፡ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ብሔር ሁሉንም ብሔረሰቦች አካተን፣ አቻችለንና ማንም ሳናገል መስራት እንዳለብን እንረዳለን፤ የክልሉ ህዝቡም ይህንን መረዳትና ማገዝ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡ "ቀደም ሲል ያልተሰሩና የነበሩ ክፍተቶች ዛሬ ላይ ችግር እየፈጠሩ ነው" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ችግሮችን ለማስተካከል አየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል ። "በአገር ደረጃ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ሰላም አስፈላጊ ነው" ያሉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሰተዳድር አቶ ገቢሳ ተስፋዬ በበኩላቸው በክልሉ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም