ግብርን የማጭበርበር ዝንባሌ የገቢ አሰባሰቡን ጎድቶታል - ኢዜአ አማርኛ
ግብርን የማጭበርበር ዝንባሌ የገቢ አሰባሰቡን ጎድቶታል
አዲስ አበባ ህዳረ 25/2011 በንግድ ማኅበረሰቡ የሕግ መተላለፍና የማጭበርበር ዝንባሌ አገሪቱ ከግብር የምትሰበስበው ገቢ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል ተባለ። የገቢ ሚኒስቴር"ግዴታዬን እወጣለሁ፤ መብቴን እጠይቃለሁ" በሚል መሪ ቃል ከመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጋር ዛሬ ተወያይቷል። የገቢ ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የአገሪቱ የግብር ገቢ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸር ከሚጠበቀው ደረጃ በታች ሆኗል። ለአብነትም የኢትዮጵያ ግብር ገቢ ከአጠቃላዩ አገራዊ ምርት ድርሻው 11 በመቶ ነው፤ ከአካባቢው አገራት የ16 በመቶ አማካይ ገቢ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነው ብለዋል። ለዚህም ደግሞ በንግዱ ማኅበረሰብ የሕግ ተገዥነት ባህል አለመዳበርና የማጭበርበር ዝንባሌ ከፍተኛ መሆኑን ነው በምክንያት ያስቀመጡት። ከፍተኛ መጠን ያላቸው ታክስ ከፋዮች ያለመመዝገብና ታክስ ከፋዮች ቢሆንም በወቅቱ የታክስ ግዴታቸውን አለመወጣትም እንደ ችግር ጠቅሰዋል። በአንዳንድ የንግድ ማኅበረሰቦች ሽያጭ ማሳነስና የተጭበረበሩ ደረሰኞችን በመጠቀም ወጪን በማጋነን ምክንያትም ገቢው ሊቀነስ ችሏል ብለዋል። የማኅበረሰቡ ደረሰኝ የመቀበል ልምድ አነስተኛ መሆንና ደረሰኝ መጠየቅ መብት ስለመሆኑን በቂ ግንዛቤ አለመኖር በንግድ ሥርዓቱ ክፍተት እንዲጎላ አድርጓም ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ግብር ከፋዮችም የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ እንዲከፍሉ ጫና አለመፍጠራቸውን ጠቅሰው ይህም የመገናኛ ብዙኃን ድክመት መሆኑን ገልጸዋል። እንደ እርሳቸው ገለጻ "ሚዲያው ለግብር አሰባሰብ መጠናከር የበኩሉን አልተወጣም፤ የገቢ አሰባሰብን በተመለከተ በዘርፉ ተቋማት ሰፊ ሽፋን አልተሰጠውም"። ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም መገናኛ ብዙሃንን በበቂ ሁኔታ እንዳልተጠቀመና ለዘርፉ ባለሙያዎችም በታክስ ዘርፍ ሥልጠና አለመስጠቱ ክፍተቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። እነዚህም ችግሮች ተጠራቅመው የግብር ገቢ አሰባሰቡ ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል ነው ያሉት። ችግሮቹን ለማቃለል ከሚመለከታው አካል ጋር በመሆን አሰራሩን ለማስተካከል እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።