ቀጥታ፡

የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ማብቃት ይገባል፤-የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር

ሀዋሳ ህዳር 25/2011 በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎና ተጠቃሚነት በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የማብቃት ሥራ መስራት እንደሚገባ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን " አካል ጉዳተኞችን በማብቃት እኩልነትና አካታችነትን እናረጋግጥ " በሚል መሪ ቃል ትናንት በሃዋሳ ከተማ ለ26ኛ ጊዜ ተከብሯል፡፡ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት አካል ጉዳተኞችን በማሳተፍና በማብቃት እኩልነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት የሁሉም የጋራ ሥራ ሊሆን ይገባል፡፡ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፍም የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ በተሟላ ሁኔታ እንዲረጋገጥ የማብቃት ሥራ ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ ይህም የአካል ጉዳተኞችን እምቅ አቅም ለመጠቀምና ልማትን ለማፋጠን ሰፊ ዕድል እንደሚፈጥር ነው የገለጹት፡፡ "ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ100 ቀናት ዕቅዱ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ በቀዳሚነት ይዟል" ያሉት ሚኒስትሯ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሁሉም የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ማካተት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በበኩላቸው ብሔራዊ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ በክልሉ ተግባራዊ መደረጉንና በእዚህም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ አካላት አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ነው የገለጹት። አካል ጉተኞችን ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ " የክልሉ መንግስት በልማት እቅዶቹ እነሱን ተጠቃሚ ለማድረግ አካቶ እየሰራ ነው" ብለዋል፡፡ መንግስት በአገሪቱ የህዝቡን 15 ከመቶ የሚሆኑ አካል ጉዳተኞችን ባካተተ መልኩ የልማት እቅዶቹን እንዲዘረጋ የጠየቁት ደግሞ የአፍሪካ የአካል ጉዳተኞች ፎረም ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ተፈራ ናቸው፡፡ በቀጣይ የሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር በተገቢው በመመዝገብ የልማት ዕቅዱ ተጠቃሚ እንዲያደርጋቸውም ጠይቀዋል፡፡ ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት መንግስት አካል ጉዳተኞችን ከሚወክሉ ማህበራትና ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄሔራዊ ማህበራት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ ናቸው። "የመሪ ቃሉ ትኩረት እኩልነትና አካታችነት ነው" ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ የ2030 የልማት አጀንዳ አካል ጉዳተኞችን የለውጡ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የደቡብ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃልጋዮ ጅሎ በበኩላቸው በክልሉ ያለውን የአካል ጉዳተኞች ብዛት፣ የጉዳት አይነትና የሚያስፈልጋቸውን አገልግሎት መለየት የሚያስችል መረጃ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡ "በቀጣይ መረጃው ተተንትኖ ለአስፈጻሚ አካላትና ፖሊስ አውጪዎች ግብዓት እንዲውል ይደረጋል" ብለዋል፡፡ በበዓሉ የተለያዩ አካላት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በአካል ጉዳተኞች የተሰሩ የተለያዩ መገልገያ እቃዎችም በአውደ ርዕይ ቀርበው ተጎብኝቷል፡፡                          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም