ቀጥታ፡

የመንዝ በግ ዝርያን በማሻሻል ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየሰራሁ ነው፤- የደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማእከል

ደብረብርሀን ህዳር 25/2011 የደብረብርሃን ግብርና ምርምር ማእከል የመንዝ በግ ዝርያን በማሻሻል ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ። ማዕከሉ በባሶ ወራናና በመንዝ ማማ ምድር ወረዳዎች ለሁለት ቀናት የአርሶ አደሮች የመስክ በዓል አካሄዷል። በማእከሉ የእንስሳት ዝርያ ማሻሻያ ተመራማሪና በሀገር አቀፍ ደረጃ የበጎች ምርምር አስተባባሪ አቶ አየለ አበበ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት ማእከሉ ባደረገው የዝርያ ማሻሻያ ስራ የመንዝ በግ ያለው ተፈጥሮአዊ ጣዕም እንደተጠበቀ ሆኖ ምርታማነትን ማሳደግ ተችሏል፡፡ ባለፉት አምስት አመታት በመንዝ ማማ ምድር ወረዳ በቀበሌ 06 በተመረጡ 60 አርሶአደሮች የበግ ዝርያውን ለማሻሻል የተከናወነው የሙከራ ስራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል። የመንዝ በግ ዝርያ ከአምስት አመት በፊት ምርታማነቱ እየቀነሰ በመምጣቱ አርሶ አደሮች ተገቢውን ጥቅም ሳያገኙ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡ በመረጣ ቴክኖለጂ በተከናወነው የዝርያ ማሻሻል ስራም የአንድ ዓመት በግ ከነበረበት ከ10 ኪሎ ግራም በታች አማካኝ ክብደት ከዕጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏል። በተጨማሪ ለእርድ ፈጥነው የሚደርሱ የዶርፐር የስጋ በጎችን ከመንዝ በጎች ዝርያ ጋር በማዳቀል የቁም ክብደቱን ማሻሻል እንደተቻለም አስረድተዋል። በዚህም የአርሶ አደሩን ገቢ ሊያሳድጉ የሚችሉ ከ14 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የበግ ግልገሎች መወለዳቸውን ጠቁመዋል። በባሶና ወራና ወረዳም ሌሎች 60 አርሶ አደሮችን በማደራጀት እስከ ስድስት ወር ዕድሜ ያላቸውን የዶርፐርና የመንዝ ዲቃላ ወንድ በጎችን የተመጣጠነ መኖ በመመገብ ክብደታቸው እንዲሻሻልና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋገጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ተቀዛቅዞ የነበረው የበግ እርባታ ሂደትም አሁን ላይ በአርሶ አደሮች ዘንድ መሻሻል መታየቱን ገልጸው በቀጣይም የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና በዘላቂነት ለማረጋገጥ የማስፋት ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የውጪ ደም ባለው የቦር ፍየል ላይ ከተጀመረው ምርምር ጎን ለጎን በመርሃ ቤቴና በምጃር ሸንኮራ ወረዳዎች በመረጣ ዝርያን የማሻሻል ስራ በቅርቡ እንደሚጀመርም አስረድተዋል፡፡ በመንዝ ማማምድር ወረዳ የ06 ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ስንታየሁ ባሻህእደር እንደገለጹት አካባቢያቸው ደጋማ በመሆኑ የሚያለሙት ሰብል በውርጭ ሲጠቃ ለችግር ይዳረጉ እንደነበር ገልጸዋል። ነባር የበጎች ዝርያ በአመጋገብና በዝምድና እርቢ ምክንያት ይደርስ የነበረውን ችግር ምርምሩ በመፍታቱ በአነስተኛ ዋጋ ይሸጡት የነበረን የስድስት ወር የበግ ግልገል ከ2ሺህ ብር በላይ በመሸጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏዋል። ባለፈው ዓመትም 16 በጎችን አድልበው ለገበያ በማቅረብ እስከ 64 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስረድተዋል። በባሶና ወራና ወረዳ በሚሊኪ ቀበሌ የማህበረሰበ አቀፍ የዶርፐር የበግ ዝርያ አርቢ ማህበር አባል ወይዘሮ በቀለች ፍቅሩ በበኩላቸው ''የአካባቢው በጎች ዝርያ ቁመናቸው አጭር በመሆኑ በገበያ ተፈላጊ አልነበሩም'' ብለዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምርምር ማእከሉ አዳቅሎ በሰጣቸው የተሻሻሉ ዝርያዎች በመታገዝ የግልገሎች እድገት በመጨመር አንድ የበግ ግልገል እስከ 3ሺህ ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ 14 አይነት የበግ ዝርያዎችና ከ25 ሚሊዮን በላይ የበግ ክምችት እንደሚገኝ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ትላንትና ዛሬ በተካሄደው የአርሶ አደሮች የመስክ በዓል ላይ አርሶ አደሮች፣ የምርምር ማዕከላት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም