የግንባታ ስራዎችን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው የቻይና ኩባንያዎች ገለፁ - ኢዜአ አማርኛ
የግንባታ ስራዎችን በቴክኖሎጂ የመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው የቻይና ኩባንያዎች ገለፁ
አዲስ አበባ ህዳሴ 25/2011 በኢትዮጵያ እየተካሔዱ ያሉ የግንባታ ስራዎችን ጥራት ማሳደግ እንዲቻል በቴክኖሎጂ የመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው የቻይና የግንባታ ኩባንያዎች ገለፁ። በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተስፋፋ የመጣው የግንባታ ኢንዱስትሪ በቴክኖሎጂ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የቴክኖሎጂ ሽግግርም እንዲፈጠር በጋራ መስራት እንደሚፈልጉ ነው ኩባንያዎቹ ለኢዜአ ያስታወቁት። በኢትዮጵያ በግንባታው ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል መልካም እድል መኖሩንም ኩባንያዎቹ ጠቅሰዋል። ኩባንያዎች ትናንት በአዲስ አበባ በተጀመረው የኢትዮጵያና የቻይና የኢንዱስትሪ ትብብር የንግድ ትርዒት ላይ በመሳተፍ ላይ ናቸው። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የሆኑት ኤለን ሊያንግ በግንባታ መሳሪያዎች ምርት ላይ የተሰማራው ድርጅታቸው መንገዶችን በጥራት ለመገንባት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት ከአገሪቱ የግንባታ ተቋራጮች ጋር ለመስራትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን የገለጹት ኃላፊው በአዲስ አበባ አንዳንድ መንገዶች ላይ የጥራት ጉድለት መታዘባቸውን ይናገራሉ። በሌላ የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና በግንባታ መሳሪያዎች ስራ የተሰማራ ኩባንያ ኃላፊ ሚንግ ሿን እንደሚሉት ደግሞ በአውሮፓና አሜሪካ ሰፊ ተቀባይነት ያለው ኩባንያቸው በኢትዮጵያም ለመሰማራት እንቀስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰዋል። በጫማ ምርት ላይ የተሰማራው ኩባንያ አስተርጓሚ አቶ ሄኖክ ጌታቸው በበኩሉ የስራ እድሎችን በመፍጠርና ቴክኖሎጂ እንዲሸጋገር እየሰራ ሲሆን ይሕን ተግባር ለማሳደግም ፍላጎት እንዳለ ነው የጠቆመው። በፀሀይ ኃይል የሚሰሩ የባትሪ ምርቶችን ከውጭ አገር በማስመጣትና በማከፋፋል ስራ የተሰማራው የኢትዮጵያ ኩባንያ ተወካይ ወይዘሪት ፍላጎት አየለ ኢትዮጵያዊያን ድርጅቶች በንግድ ትርኢቱ መሳተፋቸው ከቻይና አቻዎቻቸው ጋር በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ላይ ለመድረስ እያገዛቸው መሆኑን ገልፀዋል። በአሁኑ ወቅት 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መዋእለ ንዋይ ያፈሰሱ 602 የቻይና ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። እነዚህ ኩባንያዎች ለ38 ሺህ ቋሚና ከ41 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥረዋል።