በክፍለ-አህጉሩ አዎንታዊ ለውጥ እየታየ መሆኑን ኢጋድ ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በክፍለ-አህጉሩ አዎንታዊ ለውጥ እየታየ መሆኑን ኢጋድ ገለጸ
አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክፍለ-አህጉሩ አዎንታዊ ለውጥ እየታየ መሆኑን ገለጸ። የኢጋድ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሁለተኛው ከፍተኛ ምክክር በኡጋንዳ ካምፓላ ተካሂዷል፡፡ በዚህ ወቅት የኢጋድ ዋና ጸሃፊ አምባሳደር መሃቡብ ሙዓሊም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀጣናው አዎንታዊ ለውጥ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ መጀመሩ፣ የጂቡቲና ኤርትራ እንዲሁም የኤርትራ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ውይይት መጀመሩን ለአብነት አንስተዋል። በኤርትራ ላይ ተጥሎ የቆየው ማዕቀብ በቅርቡ መነሳቱና በደቡብ ሱዳን አንፃራዊ ሰላም መታየቱም በቀጣናው አዎንታዊ ለውጥ መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት፡፡ የኡጋንዳው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አርያም ኦኬሎ በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ለውጥ በቀጣናው በጎ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ሰላም ለማምጣት "ከባድ ነገር ግን ስኬታማ" ውሳኔ መወሰናቸውን ጠቀሰው በኤርትራ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ የሦስትዮሽ ውይይት ማስጀመራቸውንም አድንቀዋል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ሴክሬተሪ ታዬ ብሩክ በበኩላቸው በቀጣናው የተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥና ሰላማዊ ግንኙነት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ድርጅቱና ኢጋድ አጋርነታቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሻሜቦ ፌታሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የወሰዷቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች በመድረኩ አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች በከፍተኛ የመንግስት የስልጣን እርከን ላይ ቁጥራቸው እንዲጨምር መደረጉ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ የተወሰደ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል። ውይይቱ በአጠቃላይ በቀጣናው እየታዩ ባሉ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ አበረታች ለውጦች ዙሪያ መክሯል፡፡