መሬታችን የተወሰደው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከመሆኑም በላይ በቂ ካሳ አላገኘንም - የልማት ተነሺዎች

አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 መሬታችን የተወሰደው ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከመሆኑም በላይ የተሰጠን ካሳም በቂ አይደለም ሲሉ በአዲስ አበባ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የልማት ተነሺዎች ገለፁ። የከተማው አስተዳደር ከልማት ተነሺዎች ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ የአሰራር ችግሮችን ለማስተካከል አንቅስቃሴ መጀመሩ ተገልጿል። የከተማው ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ጥያቄ መሰረት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የወጣት አደረጃጀቶች ትናንት በኮዬ ፈጬ የሚኖሩት አርሶ አደሮች ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09  ኮዬ ፈጬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከ2004 ዓ.ም  ጀምሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል። ቅሬታውን ያቀረቡትም በጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ልማት ምክንያት ከአካባቢው የተነሱ አርሶ አደሮች ናቸው። ከነዋሪዎቹ መካከል  የዘጠኝ ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ታደሰ ግርማ የወረዳው አመራሮች በ2004 ዓ.ም በጋራ መኖሪያ ቤቱ ግንባታ ምክንያት የእርሻ መሬታቸውን መወሰዱንና ማረስም እንደማይችሉም የተነገራቸው በድንገት መሆኑን ገልፀዋል። "ግብረ ሃይሉ መጥቶ መሬቱን ከወሰደ በኋላ ብታርሱ 5 ሺህ ብር ትቀጣላችሁ፤ ትታሰራላችሁም" የሚል ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸውም በመግለፅ ሁኔታውን ያስታውሳሉ። በወቅቱ ለተወሰደው መሬት የተከፈላቸው ካሳም እጅግ አነስተኛ መሆኑን የሚናገሩት አርሶ አደሩ ውሳኔውም በጥናት ላይ የተመሰረተ እንዳልነበር ይገልፃሉ። ለእርሻ መሬት የተከፈላቸው ካሳ በካሬ ሜትር 18 ብር ከ50 ሳንቲም፤ ለግጦሽ መሬት ደግሞ 9 ብር ከ 25 ሳንቲም ብቻ እንደነበረ ነው አቶ ታደሰ የሚናገሩት ። በአሁኑ ወቅት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት፣ የሚያስተምሩበት፣ ቀለብ የሚችሉበት በቂ ገቢ እንደሌላቸው ጠቅሰው "መንግስት ከሚሰራው ቤት ይስጥን ወይም ሌላ አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልግልን" ብለዋል። "የእርሻ መሬታችን ተወስዶ ከቦታው እንድንነሳ መደረጉ የመኖር ህልውናችንን አደጋ ላይ የጣለ ነው" ሲሉ የገለፁት ሌላ የልማት ተነሺ አርሶ አደር አቶ ደጉ ደምሴ ናቸው። የአካባቢው አርሶአደር እየተካሄደ ባለው የልማት ሥራ ምንም ዓይነት ቅሬታ እንደሌለው የሚናገሩት አቶ ደጉ "ግንባታው ሲከናወን የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ መፈፀም ነበረበት" በማለት አብራርተዋል። መሬታቸውን ማጣታቸው በአሁኑ ወቅት ከተፈጠረው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ኑሮ ከባድ ፈተና እንደሆነባቸውም አንስተዋል። መንግስት በአካባቢው ፋብሪካ በመገንባት ወይም ሌሎች የስራ እድል የሚፈጥሩ ተግባራትን በማከናወን የአካባቢውን ህዝብ ኑሮን መደገፍ እና ተጨማሪ የሞራል ካሳ መክፈል እንዳለበት አሳስበዋል። ሌላኛዋ አርሶ አደር ወይዘሮ ብርቄ ሻኔ በበኩላቸው የኑሮ ውድነቱ በስራቸው ያሉ 8 ልጆችን መቀለብ ከአቅም በላይ ስለሆነባቸው አረቄና ጠላ በመሸጥ ኑሯቸውን ለመደጎም ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ነው የገለፁት። ከግብርና ውጪ ሌላ ኑሮን በአግባቡ ለመምራት የሚችሉበት መንገድ እንደሌለ ጠቅሰው የቤተሰባቸውን ህይወት ለማቆየት ሲሉ  ማታ ማታ በድብቅ ለማረስ መገደዳቸውንም ተናግረዋል። ከጉብኝቱ በኋላ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የወጣት አደረጃጀቶች በአካባቢው የታዘቡትን ለምክትል ከንቲባው አቅርበው ውይይት ይካሄዳል ቢባልም ውይይቱ ለሌላ ጊዜ ተራዝሟል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክተል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከትናንት በስቲያ የልማት ተነሺ ከሆኑ የከተማዋ አርሶ አደሮች ጋር በቀጣይ ህይወታቸውን ማሻሻል በሚችሉበት ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። በውይይቱ ወቅት ምክትል ከንቲባው የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ያነሱት ጥያቄ "ትክክለኛና በመንግስት የተፈጠረ ስህተት" መሆኑን ገልጸዋል። የልማት ተነሺ አርሶ አደሮች መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ስራውን በአግባቡ እያከናወነ ባለመሆኑ እንደገና ለማደራጀትም ስራው ተጀምሯል ብለዋል። "በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተፈጠረው የትናንቱ ስህተት አይደገምም" ያሉት ምክትል ከንቲባው አርሶ አደሮች ከቤተሰቦቻቸው ጋር በአንድ አካባቢ አብረው የሚኖሩበት አሰራር እንደሚፈጠር የለገሃርን የተቀናጀ መንደር ግንባታን በማሳያነት በመጥቀስ አብራርተዋል። በልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ስም ሀሰተኛ ማስረጃ ይዘው የሚመጡ አካላት እንዳሉና "ህገ ወጥነትን ለመከላከል ከጎናችን እንድትሆኑ" ሲሉም ጠይቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም