ቀጥታ፡

አቶ ተፈራ መኮንን የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ዋና ጸሃፊ ሆኑ

አዲስ አበባ ህዳር 25/2011 የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዳይሬክቶሬት ጄኔራል የነበሩት አቶ ተፈራ መኮንን የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ሆነው ተመረጡ፡፡ ኮሚሽኑ ትናንት በዛምቢያ ሊቪንግስተን ከተማ ባደረገው ስብሰባ ኢትዮጵያ በዕጩነት ያቀረበቻቸውን አቶ ተፈራ መኮንን መመረጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ኢትዮጵያ ያቀረበችው ዕጩ መመረጥ ለቀጣናው ወሳኝ ፋይዳ እንደሚኖረውም ገልጿል። በቅርቡ በተካሄደው 11ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ልዩ ጉባኤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከአፍሪካ አቻዎቻቸው ጋር በመገናኘት ግለሰቡ እንዲመረጡ ማግባባታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውሷል። ዶክተር ወርቅነህ አፍሪካዊያን በኢትዮጵያ ላሳዩት የመተማመን መንፈስና ወገንተኝነት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። አፍሪካ የሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1964 በአዲስ አበባ በተካሄደው የአፍሪካ እንድነት ድርጅት ጉባኤ የተቋቋመ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ስራውን የጀመረው እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1969 ነው፡፡ ዋና መቀመጫውም ሴኔጋል ዳካር ይገኛል። አቶ ተፈራ መኮንን በአቪዬሽን ስራ የ37 ዓመት ልምድ ያካበቱ ሲሆን በኬንያ ናይሮቢ የዓለም አቀፍ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ፕሮጀክት ኃላፊ፤ እንዲሁም በአፍሪካ የሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን የትራንስፖርት ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። በካናዳ ሞንትሪያል በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ በመሆንም ለስምንት ዓመታት አገልግለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም