የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ለሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት አዲስ አበባ ገብተዋል

7
ግንቦት 17/2010 የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ በኢትዮጵያ ለሚያደርጉት የሶስት ቀናት ይፋዊ ጉብኝት ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል። ፕሬዚዳንቱ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ እና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ፖል ካጋሜ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ጋር በሁለትዮሽ፣ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ። የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት የመስክ ጉብኝት እንደሚያደርጉም ይጠበቃል። ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ የተጋበዙ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ መሆናቸውን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም