ኮሚሽኑ አገልግሎቱን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየሰራ ነው

81
አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አገልግሎቱን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገለፀ። የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተካ ገብረየስ ለኢዜአ እንዳሉት ኮሚሽኑ አገልግሎቱን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ሁለት የቴክኖሎጂ ፕሮጀክቶችን በአጋሮቹ አማካኝነት እያለማ ነው። "አይ ጋይድ ኢትዮጵያ" የተሰኘው ቴክኖሎጂ ባለሃብቶች ምን አገልግሎት የት፣ ከማንና እንዴት እንደሚያገኙ በግልጽ የሚያስቀምጥና በይነ-መረብን ተጠቅመው  ሊያገኙት የሚችሉት መሆኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም ከኮሚሽኑም ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት አገልግሎቶችን ለማግኘት ማድረግ የሚገባቸውንና ማሟላት የሚጠበቅባቸውን መረጃዎች የያዘ እንደሆነም አብራርተዋል። ፕሮጀክቱ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተባበሩት መንግስታት የንግድና ልማት ምክር ቤት ድጋፍ የለማና ለአገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በሙሉ ማቅረብ የሚያስችል እንደሆነም አስረድተዋል። "ኢ አይ ሲ ኦንላይን ሲስተም"  የተሰኘው ሌላኛው ፕሮጀክት ደግሞ በአለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የለማ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አገልግሎቶችን መስጠት የሚያስችል ደረጃውን የጠበቀ አሰራር ነው ብለዋል። ይህ አሰራር ከፊርማ በስተቀር ባለሃብቶች ማሟላት ያለባቸውን መረጃዎች እንዲያስገቡ የሚያደርግ መሆኑንም ነው ያስረዱት። ፕሮጀክቶቹ በቅርብ ወራት ወደትግበራ እንደሚገቡም ነው ምክትል ኮሚሽነሩ የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም