የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ በትኩረት እንሰራለን - ተመራቂ ሴት የህክምና ዶክተሮች

85
ሀዋሳ ህዳር 24/2011 የእናቶችና ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ለሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ሴት የህክምና ዶክተሮች ገለጹ፡፡ በሃገሪቱ የተጀመረው ሴቶችን ወደ ከፍተኛ አመራር የማምጣት ሂደት የበለጠ እንዲሰሩ መነሳሳት እንደፈጠረባቸው አስተያየት ሰጪዎቹ ገልፀዋል፡፡ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለ5ኛ ጊዜ የህክምና ዶክተሮችን ሲያስመርቅ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ሴቶች በተመረቁበት ሙያ ሃገራቸውን ለማገልገል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡ ዶክተር ትእግስት ገረሱ 3 ነጥብ 46 አምጥታ የሴቶችን ከፍተኛ ውጤት በመያዝ ተሸላሚ ስትሆን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ለውጤት መብቃቷንና ህብረተሰቡን ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች፡፡ የእናቶችና ህጻናትን ሞት ላይ መመረቂያዋን እንደሰራች ገልጻ በቀጣይም እንደ ሴት በዚህ ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራትን ለመቀነስ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ የድርሻዋን እንደምትወጣ ገልጻለች፡፡ ''ዓላማ ያላቸው ሴቶች ትልቅ ቦታ የመድረስ አቅም አላቸው'' ያለችው ዶክተር ትእግስት በሃገሪቱ አመራርነት ቦታ ላይ መምጣታቸው ለበለጠ ስራ እንዳነሳሳት ተናግራለች፡፡ ሌላኛዋ ተመራቂ ዶክተር ሰላማዊት ጌትነት በበኩሏ መንግስት በሚመድባት በገጠሪቱ የሃገሪቱ ክፍል ስትሰማራ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ያገኘችውን እውቀት ተጠቅማ ለማገልገል ተዘጋጅታለች፡፡ በዩኒቨርቲው የመጨረሻ ዓመት የተግባር ልምምድ በርካታ እናቶች ሪፈር ተደርገው እንደሚመጡ ገልጻ በቀጣይ የማህጸንና ጽንስ ሃኪም በመሆን የእናቶችን ሞት ለመቀነስ እንደምትሰራ ገልጻለች፡፡ እናቶች በቅርበት አገልግሎት አግኝተው መዳን በሚችሉት በሽታ ሪፈር እንደሚደረጉ የገለጸችው ዶክተሯ የባለሙያና ግብዓት እጥረት ለእናቶች ሞት ምክንያት በመሆኑ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁማለች፡፡ ''ሴቶች በአመራር የበለጠ ድርሻ ሲኖራቸው ጥቅሙ ብዙ ነው'' የምትለው ተመራቂዋ በአመራርነትም ሆነ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተሻሻለ የመጣውን ቁጥር በማሳደግ በሃገር ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ገልፃለች፡፡ “ከመመረቄ አስቀድሞ በተግባር ልምምድ ወቅት ህብረተሰቡን ማገልገል ጀምሬያለሁ” የምትለው ሌላኛዋ የእለቱ ተመራቂ ደግሞ ዶክተር ተስፋነሽ ተመስጌን ናት፡፡ ''ከወሊድ ጋር ተያይዞ በእናቶች ላይ የሚደርሰውን ሞት ለመቀነስ እንደ ሴት የበለጠ ኃላፊነት አለብን' በትኩረትም ልንሰራው ይገባል'' ብላለች፡፡ በምረቃው ወቅት በክብር እንግድነት የተገኙት የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስተሯ ያስተላለፉት መልእክት መነሳሳትን እንደፈጠረባት ተናግራ ''መንግስት በአሁን ወቅት ለሴቶች የሰጠው የአመራርነት ሚና የበለጠ እንድንሰራ የሚያደርግ ነው'' ብላለች፡፡ በእለቱ ከተመረቁ 76 የህክምና ዶክተሮች መካከል 18ቱ ሴቶች ሲሆኑ የክብር እንግዳዋ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም አነቃቂ ንግግር አድርገዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም