ጅማ አባ ጅፋር የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ጅማ አባ ጅፋር የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ያደርጋል
አዲስ አበባ ህዳር 24/2011 ጅማ አባ ጅፋር በ2018/19 የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ከጂቡቲ ቴሌኮም ጋር ያደርጋል። የውድድር ዓመቱ የሻምፒዮንስ ሊጉ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይደረጋሉ። በአሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ የሚሰለጥነው ጅማ አባ ጅፋር ከጂቡቲው ጂቡቲ ቴሌኮም ጋር ጨዋታውን ያደርጋል። ህዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በስታድ ዱ ቪል በተደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ተጋጣሚውን 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፎ መመለሱ ይታወሳል። ለጅማ አባ ጅፋር አስቻለው ግርማ አንድና ማሊያዊው ማማዱ ሲዲቤ ሁለት ጎሎች አስቆጥረዋል። ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳው ውጭ ያስመዘገበው ውጤት የማለፍ እድሉን ከፍ አድርጎታል። ክለቡ በ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ እየተወዳዳረ በሚገኝበት የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር በመጀመሪያው ጨዋታ ከሜዳው ውጭ በማሸነፍ ጅምሩን መልካም አድርጓል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታን ኬንያዊው ፒተር ዋዌሩ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል። ጅማ አባ ጅፋር የደርሶ መልስ ጨዋታውን ካሸነፈ ከባለፈው ዓመት የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍጻሜ ተፋላሚ ከነበረው የግብጹ አል አህሊ ጋር በታህሳስ ወር 2011 ዓ.ም ይጫወታል። በሌላ በኩል መከላከያ በ2018/19 አፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 10 ሰአት ከናይጄሪያው ኢኑጉ ሬንጀርስ ጋር ያደርጋል። በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚሰለጥነው መከላከያ ህዳር 19 ቀን 2011 ዓ.ም በናምዲ አዚኪዌ ስታዲየም ባደረገው የመጀመሪያ ጨዋታ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት መሸነፉ የሚታወስ ነው።