በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አውደ ርዕይ ተዘጋጀ

83
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተኪ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት ያላቸውን አቅም እንዲያጎለብቱ የዘርፉን አምራቾች መደገፍ እንደሚገባ ተገለጸ። በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አውደ-ርዕይ ተዘጋጅቶ ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በተገኙበት ተከፍቷል። የአውደ-ርዕዩ ዋና ዓላማ አገር ውስጥ የሚገኙ የዘርፉ አምራቾች እርስ በእርስ በመተዋወቅ ምርቶቻቸውን እንደ ግብዓት የሚለዋወጡበትን የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሆነም ተገልጿል። አገሪቷ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር እየገባች ባለበት በአሁኑ ወቅት ለዘርፉ ማነቆ የሆኑ በርካታ ችግሮች ሳይበግራቸው ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ምርት አምርተው ላቀረቡት አምራቾች ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዶክተር አምባቸው መኮንን በበኩላቸው መንግስት ለአምራቾች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ የዶላር ምንዛሬ እጥረትን ጨምሮ  የሚያጋጥሙ የዘርፉ ማነቆዎችን ለመፍታት የተቋቋሙ የመንግስት ተቋማትና ኢንስቲትዩቶች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል። በመድረኩ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾች በዘርፉ እያጋጠሟቸው ያሉ ችግሮችን በማህበራት ተወካዮቻቸው በኩል አቅርበው፤ መንግስት ጥያቄያቸውን ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል። በአገር አቀፍ ደረጃ ከሁለት ሺህ አምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 150 ያህሎቹ በአውደ-ርዕዩ የተሳተፉ ሲሆን፤ እነዚህም አምራቾች ላቅ ያለ ምርቶችን ያመረቱና በገቢ ደረጃቸውም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ የተሸጋገሩ ናቸው። አውደ ርዕዩ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስተባባሪነት፣ በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በጋራ የተዘጋጀ ሲሆን ለቀጣዮቹ ስድስት ቀናት ክፍት ሆኖ ይቆያል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም