በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ወባን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑ ተጠቆመ

66
ሀረር ግንቦት 16/2010 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በመንግስትና በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ወባን ለመከላከል በተከናዎኑ ሥራዎች በአካባቢያቸው በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን የባቢሌና የሐረማያ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። በዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ወባማ በሆኑ ስድስት ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር ከ280 ሺህ የሚበልጥ የአልጋ አጎበር መሰራጨቱን የዞኑ ጤና ጥበቃ ቢሮ አስታውቋል። በባቢሌ ከተማ ቀበሌ 04 የሚኖሩት ወይዘሮ ፋጡማ አልይ እንዳሉት የወባ በሽታ ስርጭት በአንድ ወቅት በአካባቢው ጠፍቶ የነበረ ቢሆንም በ2007 ዓ.ም ዳግም ተከስቶ በበሽታው እርሳቸውን ጨምሮ ብዙ ሰዎች መጠቃታቸውን ተናግረዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት በመንግሰት በኩል የኬሚካል ርጭትና የአጎበር ስርጭት ሥራ ከመስራቱ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ ውሃ የሚያቁሩ ሥፍራዎችን የማጽዳት ሥራ ማከናወኑ በአካባቢያቸው በወባ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸዋል። ከሚያዚያ ወር ጀምሮ በአካባቢያቸው የወባ በሽታ እንደሚከሰት ያስታወሱት የሐረማያ ከተማ ነዋሪው አቶ ረሺድ መሀመድ በበኩላቸው ወባን ለመከላከል ከአልጋ አጎበር በተጨማሪ ቤታቸውን ኬሚካል እንደሚያስረጩ ገልጸዋል። "ከዚህ በተጨማሪ የበሽታውን ምልክት ስናይ ወደ ጤና ጣቢያ በመሄድ በአካባቢያችን በወባ በሽታ የሰዎች ሕይወት ማለፍ በእጅጉ ቀንሷል" ብለዋል። በሽታው በአንድ አካባቢ ሲከሰትና ሲታይ ብቻ ለመከላከል የሚደረገው ጥረት በቂ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ተሺድ፣ በየጊዜው ተገቢ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል። "በአካባቢና የግል ንጽህና አጠባበቅ ለ435 አባውራዎች ትምህርት እሰጣለሁ፤ በሽታን አስቀድሞ የመከላከል ስራም ከህብረተሰቡ ጋር አከናውናለሁ" ያለቸው ደግሞ የባቢሌ ከተማ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዋ ወይዘሮ ሮማን አመሐ ናት። የወባ ስርጭትን ለመከላከል ለአንድ አባውራ ሁለት የአልጋ አጎበር ከመስጠት ባለፈ በአጠቃቀሙ ላይ የሕብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራ እንደሚሰሩ አመልክታለች። ውሃ ያቆሩ አካባቢዎችን ከማፋሰስና ከማዳፈንና ባለፈ የጸረወባ ኬሚካል ርጭት ሥራ በመከናወኑ በአካባቢው የወባ በሽታ ስርጭት በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱን ተናግራለች። በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ጤና ጥበቃ ቢሮ የወባ በሽታና ስርጭት መከላከል ኃላፊ አቶ አለማየው ከበርኩ በበኩላቸው ወባማ በሆኑ ስድስት የዞኑ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከ280 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበር ባለፈው ሚያዚያ ወር መሰራጨቱን አስታውሰዋል። በ83 ጤና ኬላዎች በሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞች አማካኝነት በተከናወነው ወባን የመከላከል ሥራም ከ108 ሺህ በላይ አባወራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መቻሉን ገልጸዋል። በዞኑ የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በተከናወኑ ሥራዎች በየዓመቱ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል። ለዚህም ባለፈው በጀት ዓመት በዞኑ በወባ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 15ሺህ 423 የነበሩ ሲሆን ዘንድሮ ይህ ቁጥር ወደ 3ሺህ መቀነሱን በማሳያነት ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም