የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ እንዲሰማሩ ተወሰነ

46
አዲስ አበባ ህዳር 22/2011 የኢፌዲሪ የብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን የጸጥታ ችግሮች በመፍታት የህግ የበላይነትን ለማስከበር የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት እንዲሰማሩ ወሰነ። የብሄራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ዛሬ ማምሻውን "የህግ የበላይነት በማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን የህዝብ ደህንነትን ማስከበር የመንግስት ቀዳሚ ተግባር ነው! ህገ ወጦችን ወደ ህግ የማቅረቡ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል!" በሚል ርዕስ መግለጫ ማውጣቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይፋ አድርጓል። በዚሁ መግለጫው እንዳስታወቀው፤ የመንግስት ቀዳሚ ተግባር የህዝቦችን ደህንነት መጠበቅና የህግ የበላይነትን ማስከበር ነው። በዚህ መሰረት በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የታዩትን የጸጥታ ችግሮች በመፍታት ሰላም በማስከበርና የዜጎችን ህይወት በመታደግ የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት በአካባቢው የማረጋጋት ተግባራትን ያከናውናሉ። በተጨማሪም በአካባቢው ያለውን ማንኛውንም ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በመቆጣጠር ተጠርጣሪዎችን ወደ ህግ እንደሚያቀርቡ መግለጫው አብራርቷል፡፡ ምክር ቤቱ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እና ሰብዓዊ ቀውስ በማስመልከት ከክልሎቹ መንግስታት ጋር ዛሬ በጥልቀት መክሯል። በውይይቱ ወቅት የአካባቢውን ሰላም የማስከበር፣ የዜጎችን ህይወት የመታደግ፣ የህግ የበላይነት በማስከበር አስተማማኝ ሰላም እና ጸጥታን የማስፈን ጉዳይ ከሁለቱ ክልሎች አቅም በላይ ስለመሆኑ ግንዛቤ መያዙን ነው መግለጫው ያብራራው። ክልሎቹም የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት በህገ መንግስቱ መሰረት ጣልቃ ገብተው ችግሩን እንዲያረጋጉ ጥያቄ ማቅረባቸውን የጠቆመው የምክር ቤቱ መግለጫ፤ የጸጥታ አካላቱ በአካባቢው ተሰማርተው የህግ የበላይነት እንዲያስከብሩ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደ ቤትና ንብረታቸው በመመለስና በማቋቋም ሰላም እንዲያሰፍኑ መወሰኑንም ነው ያረጋገጠው። የምክር ቤቱ መግለጫ እንዳመለከተው፤ በአሁኑ ወቅት ጥቅማቸው የተነካ የተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ለማደናቀፍ፣ በህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና የመረዳዳት ባህል ተሸርሽሮ በምትኩ ቂምና ቁርሾ እንዲሰፍን፣ ግጭት ተከስቶ ሞት፣ መፈናቀል እና ሰብዓዊ ቀውሶችን በማስፋፋት ለውጡን ለመቀልበስ እየሰሩ ናቸው። እነዚህ አካላት እየሰረቁ፣ እየዘረፉ እና ሰብዓዊ መብቶችን እንዳሻቸው እየጣሱ ያለተጠያቂነት መኖር የሚያስችላቸውን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ነው ምክር ቤቱ  ያተተው። መንግስት ህግን በማስከበር በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በአገር ሀብት ዝርፊያ በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ መውሰድ የጀመረውን እርምጃ አቅጣጫ ለማሳት እና ለመቀልበስ ሲረባረቡ እንደሚስተዋል ያመለከተው መግለጫው፤ እነዚህ ኃይሎች የተጀመረውን ለውጥ በማደናቀፍ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠብቅ ሲሉ የብዙ ንጹህ ዜጎችን ሰላምና የአገርን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣል በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙም አትቷል። እነዚህ ኃይሎች ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ግጭቶችን በመቀስቀስ በሰዎች ህይወትና ንብረት ላይ "ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል፤ ብዙዎችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል" በማለት ገልጿል። ይህን ችግር በማስወገድ ለግጭቶቹ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች ወደ ህግ ለማምጣት እየሰራ መሆኑን ገልጾ፤ በችግርና በእንግልት ላይ ላሉ ዜጎችም ድጋፍ ለማድረግ መንግስትም ህዝብም በማስተባበር ሰፊ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን አስታውሷል። መንግስት የህግ የበላይነትንና የህዝቦችን ደህንነት ለማረጋገጥ የጀመረውን ተግባር ከመቼውም ጊዜ በላይ በበለጠ ሃለፊነት እንደሚወጣ አመልክቶ፤ ተግባሩ በሌሎች ክልሎችም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥቷል። ህዝቡ ከመንግስት ጎን በመቆም ለውጡን እውን ለማድረግ የማይተካ ሚናውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ጥሪውን አስተላልፏል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም