የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ
አዲስ አበባ ህዳር 21/2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ይካሄዳሉ። የ2011 ዓ.ም የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከጥቅምት 25 ቅን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በብሔራዊ ቡድኖች ዝግጅት፣ በክለብ ውድድሮችና በሌሎች ምክንያቶች ተቋርጠው መቆየታቸውና ለሌላ ጊዜ መተላለፋቸው ይታወቃል። የሊጉ የአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብሮች ነገ እና ከነገ በስቲያ ጀምሮ መካሄዳቸውን ይቀጥላሉ። በዚህም መሰረት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከደቡብ ፖሊስ ነገ በ9:00 ሰዓት በትግራይ ስታዲየም ይገጥማሉ። ፋሲል ከነማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ ወላይታ ድቻ ከመቀሌ ሰብአ እንደርታ፣ ባህርዳር ከተማ ከሐዋሳ ከተማ እንዲሁም አዳማ ከሲዳማ ቡና እሁድ በተመሳሳይ 9:00 ሰዓት በክልል ስታዲየሞች የሚካሄዱ ጨዋታዎች ናቸው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከስሑል ሽረ ደግሞ እሁድ በ10:00 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያካሄዳሉ። ጅማ አባጅፋር ከድሬዳዋ ከተማ እና ደደቢት ከመከላከያ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል። በዚሁ መሰረት ጨዋታቸው ሳይደረጉ የተራዘሙት መርሃ ግብሮች በተስተካካይ ጨዋታዎች እንደሚያዙና ጨዋታዎቹ የሚካሄዱበት ጊዜም በቀጣይ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል። በሌላ በኩል በብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅቶችና ሌሎች ምክንያቶች ያልተካሄዱ ቀሪ የሁለተኛና ሶስተኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ወደፊት በሚገለጹ ቀናት ይከናወናሉ ተብሏል። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች መቐለ ሰብአ እንደርታ፣ ኢትዮጵያ ቡናና ሐዋሳ ከተማ በእኩል ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።