የአካል ጉዳተኞችን ሁለንትናዊ መብቶች ለማስከበር አስፈጻሚ አካላት ግንባር ቀደም ሚና አንዲጫወቱ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
የአካል ጉዳተኞችን ሁለንትናዊ መብቶች ለማስከበር አስፈጻሚ አካላት ግንባር ቀደም ሚና አንዲጫወቱ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ ህዳር 21/2011 በኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞችን ሁለንትናዊ መብቶች ለማስከበርና የአኗኗር ሁኔታን ለማሻሻል የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ። ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን "አካል ጉዳተኞችን በማብቃት አካታችነትንና እኩልነትን እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በመጪው ህዳር 24 ቀን 2011 ይከበራል። የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኖች ብሔራዊ ማህራት ፌዴሬሽን ዛሬ መግለጫ ስጥተዋል። በሚኒስቴሩ የህዝብ ግኑኙነት ዳሬክተር አቶ አሰፋ ይርጋለም እንደገለጹት፤ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ የሚስተዋለውን የተዛባ አመለካከት በማስወገድ የጉዳተኞቹን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኛ ዜጎች ሰብአዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ መብቶችና ጥቅሞች እንዲከበሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ ገልጸዋል። አካል ጉዳተኞች ለሁለንትናዊ መብቶቻቸው መረጋገጥና የአኗኗር ሁኔታ እንዲሻሻል አስፈጻሚ አካላት ግንባር ቀደም ሚና አለባቸው ነው ያሉት። ማህበራት፣ በአካል ጉዳተኞች ዙሪያ የተሰማሩ ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ እንዲሁም የሚዲያ አካላትና ሁሉም ህብረተሰብ በተቀናጀ መልኩ በመስራት የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊና ምጣኔ ኃብታዊ ችግሮች በጋር ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል። የአካል ጉዳተኞችን ከተረጂነት በማውጣት በአገሪቱ ልማት የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱበት ስልት መቀየስ እንደሚቻልም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኖች ብሔራዊ ማህራት ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ምህረት ንጉሴ በበኩላቸው፤ በመንግስታቱ ድርጅት የተቀየሰውን ዘላቂ የልማት ግብ ትግበራ ለማፋጠን የአካል ጉዳተኞች ሚና የራሱ የሆነ ድርሻ አለው ብለዋል። በኢትዮጵያ ለ26ኛ ጊዜ የሚከበረው የዓለመ አካል ጉዳተኞች ቀን የዘንድሮው በዓል ህዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ረእሰ መዲና ሀዋሳ ከተማ በድምቀት ይከናወናል።