በኢትዮጵያ ማርን በብዛትና በጥራት ለማምረት ንብን በዘመናዊ መንገድ ማነብ ይገባል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ማርን በብዛትና በጥራት ለማምረት ንብን በዘመናዊ መንገድ ማነብ ይገባል ተባለ
አዲስ አበባ ህዳር 21/2011 በኢትዮጵያ ንብን በዘመናዊ መንገድ በማነብ የአገሪቱን የማር ምርት ለማሳደግ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ። በአገሪቱ ማርን በብዛትና በጥራት ለማምረት የንብ እርባታ ኢንዱስትሪ መቋቋም ይኖርበታል ተብሏል። በኢትዮጵያ ከመቶ ዓመት በላይ የንብ ማነብ ልምድ ቢኖርም አሰራሩ ባህላዊ መንገድ የተከተለ በመሆኑ የሚፈለገውን ያህል የማር ምርት ማምረትና ለገበያ ማቅረብ አልቻለችም። በአገሪቱ ከ2 ሚሊየን በላይ ንብ አናቢዎች ያሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በዓመት እስከ 50 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማር በመመረት ላይ ይገኛል። ያም ሆኖ ግን የአመራረት ስርዓቱ እንዲዘምን ቢደረግ በአገሪቱ ከዚህ የበለጠ መጠን ማር ማምረት እንደሚቻል ነው ዛሬ አዲስ አበባ በተጀመረውና በዓለም አቀፉ አናቢዎች ፌዴሬሽን (Apimondia) በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተመለከተው። ጉባኤው "በምግብ ምርት ላይ የንቦች አስተዋጽኦ" በሚል ርዕስ እየተካሄደ ባለው ጉባኤ ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን የንብ እርባታ ለዜጎች ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ከመሆን ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ዓይነተኛ ሚና እንዳለውም ገልፀዋል። ሆኖም በኢትዮጵያ በርካታ የንብ ዝርያዎችና በሚሊዬን የሚቆጠሩ አናቢዎች ቢኖሩም በተለያዩ ችግሮች ሳቢያ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን እያገኘች እንዳልሆነ ነው የተናገሩት። በመሆኑም መንግስት ገበያ ተኮር የማር ምርት ለማምረት በዘርፉ ከተሰማሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአለም የንቦች ቁጥር እየተመናመነ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ችግሩን ለመከላከል ከአለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብረ መስራት የግድ መሆኑን አስረድተዋል። የአየር ንብረት መዛባት፣ በሽታና የተክሎች መጠን መመናመን ለንቦች ቁጥር እንዲቀንስ ካደረጉት ምክንያቶች መካከል የችግሩ መንስኤ በመሆኑ የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይኖርብናል ብለዋል። ለንቦች ቁጥር መመናመን አንዱ ምክንያት የሆነው በአርሶ አደሩ ዘንድ በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ላለው የጸረ አረም ርጭት ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል። በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ እድገት እያሳየ ያለውን የግብርና ዘርፍ ዘመናዊ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት አነስተኛ እንደሆነም ሚኒስትሩ አክለዋል። በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ዓለም አቀፍ ጉባኤም መንግስትን፣ በዘርፉ የተሰማሩ አናቢዎችን፣ ማህበራትና ተቋማትን የሚያበረታታ ነው ብለዋል። የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሊድ ቦምባ በኢትዮጵያ የማር ምርትን ለማሳደግ አሰራሩን ዘመናዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል። በአገሪቱ ማርን በብዛትና በጥራት ለማምረት የንብ እርባታ ኢንዱስትሪ መቋቋም አንዳለበትም አሳስበዋል። ዘርፉን ማሳደግ አንዲቻል አዳዲስ ቴክኖሎጂ ማላመድ፣ ዛፎችን በብዛት መትከል፣ የገበያ ትሰስር መፍጠር፣ አመራረቱን ዘመናዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ዓለም አቀፉ አናቢዎች ፌዴሬሽን (Apimondia) ምክትል ፕሬዚዳንት ፒተር ኮዝሙስ ኢትዮጵያ ካላት የማምረት አቅም አኳያ አሁን ያለው ምርት ከ10 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጸዋል። የአየር ንብረት ለወጥ፣ የንቦች በሽታ እና የአለም ገበያ መለዋወጥ የዘርፉ ችግር በመሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ውይይት ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል። "ንቦች ከሌሉ ህይወት የለም" የሚሉት ምክትል ፕሬዘዳንቱ ተመራማሪዎች፣ እውቀት ያላቸው ሰዎች ልምዳቸውን ማካፈል አለባቸው ብለዋል።