ቀጥታ፡

ሰላምን የሚመጥን ዋጋ የለምና እንከባከበው--ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ

አክሱም ህዳር 21/2011 የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝቦች በጋራ የሀገርን ሰላም ፍቅርና አንድነት ሊጠብቁ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያሪክ ብጾዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ገለጹ። የአክሱም ህዳር ጸዮን በአል ከመላው ሃገሪቱና ከኤርትራ የመጡ በርካታ የዕምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል። በበዓሉ ላይ ፓትሪያርኩ እንደተናገሩት የዘንድሮው የህዳር ጽዮን በዓል ለዓመታት ተለያይተው የቆዩት ሁለቱ ሲኖዶሶች አንድ ላይ ከኤርትራዊያን ወገኖች ጋር ያከበሩት በመሆኑ የተለየ ያደርገዋል። “ሰላም ስላለ ነው በዓሉን እያከበርን ያለነው ሰላም ከሌለ ምንም ነገር የለም ለሰላም የሚመጥን ዋጋ የለውም” ያሉት ፓትሪያርኩ ሰላም ትልቅ ሃብትና ጸጋ መሆኑን በመገንዘብ ህዝቡ ጸንቶ መጠበቅ እንዳለበት ተናግረዋል። “ሀገሪቱ የሰላም የፍቅር የአንድነት የመረዳዳት ሀገር ናት አሁን በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮች መወገድ አለባቸው ህዝብና መንግስት የሀገር አንድነትና ሰላምን ሊጠብቁ ይገባዋል” ብለዋል። የኢትዮጵያ ህዝብም የችግሩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ መራራቅን ማራቅ እንዳለበት እና ለሰላም እና ለአንድነታችን መጽናት እንዳለበት ገልጸዋል። የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው የህዳር ጽዮን በአል ከሁለት ሺህ በላይ ዘመናትን ያስቆጠረ ኃይማኖታዊ በዓል ነው። አማኞች ህዳር ጽዮንን በአክሱም ልደትን በላሊበላ ጥምቀትን በጎንደር እና ሌሎችንም በዓላት ከወገኖቻቸው ጋር በድምቀት ሲያከብሩ ቢኖሩም አሁን ላይ በሃገሪቱ እየተስተዋለ ያለው የዜጎች የመንቀሳቀስ ህገ-መንግስታዊ መብት ስጋት እንደገጠመው ተናግረዋል። ኢትዮጵያዊያን በባህል በቋንቋ በሃይማኖት እና በኑሮ የተዛመዱና ተዋህደው የኖሩ መሆናቸውን ተናግረው መከባበርና አንድነት እንዲጠፋ የሚሰሩ ሃይሎችን በጋራ መታገል አንደሚያስፈልግ ዶክተር ደብረጽዮን ተናግረዋል። ከኤርትራ ለመጡ አንግዶች የአንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት ምክትል ርዕሰ-መስተዳደሩ ሁለቱም ሀገራት የጀመሩት ግንኙነት ለማጠናከር ህዝብን የሚጠቅም ስምምነት በመፍጠር በትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል። በበአሉ ላይ የተገኙት የኃይማኖት አባቶችና ምዕመናን በሀገሪቱ ሰላም ፍቅርና አንድነት አንዲሰፍን የምህላ ጸሎት አድርገዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም