በድሬዳዋ በዕቅድ ዘመኑ ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተጠቆመ

ድሬዳዋ ግንቦት 16/2010 በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት የገጠሩ ሕብረተሰብ በኢኮኖሚና በማህበራዊ አገልግሎቶች  ተጠቃሚ ቢሆንም ወጣቶችን የሥራ ዕድል ባለቤት ከማድረግ አንጻር ውስንነት መኖሩን የድሬዳዋ አስተዳደር ገጠር ነዋሪዎች ተናገሩ። በዕቅዱ የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ  ውይይት ሲደረግ ነዋሪዎቹ እንዳሉት ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል የጎላ ክፍተት በመኖሩ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። በአስተዳደሩ የዋሂል የገጠር ቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ መሀመድ እንዳሉት ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የገጠሩ ሕብረተሰብ በአካባቢው የትምህርት፣ የጤናና የመንገድ አገልግሎት በማግኘቱ ተጠቃሚ ሆኗል። የመስኖ ልማት ተደራሽነት እያደገ በመሆኑም በአካባቢያቸው የተወሰኑ ሰዎች የልማቱ ተጠቃሚ በመሆን ገቢያቸውን በማሳደግ ላይ መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡ በአሁኑ ወቅትም የመንገድ ውስኑነት መኖሩን የገለጹት አቶ አህመድ፣ በአካባቢው ለወጣቱ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግሮችን ለመፍታት ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል። የለገኦዳ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ አቶ መሐመድ አብዱላሂ በዕቅድ ዘመኑ የገጠሩን ሕብረተሰብ ለመለወጥ የተደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም በሪፖርት የቀረበውና በተጨባጭ መሬት ላይ የተሰራው አንደማይጣጣም ጠቁመዋል። ወጣት ዚያድ አደም በበኩሉ "ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ የገጠሩን ወጣቶች የሥራ ዕድልና የተዘዋዋሪ ገንዘብ ብድር አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የተደረጉ ጥረቶች በገጠር ካለው የሥራ አጥ ወጣቶች ቁጥር ብዛት አንጻር አነስተኛ ነው" ብሏል፡፡ ተደራጅተውና ሰልጥነው ወደሥራ ለመሰማራት በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙት በርካታ ወጣቶች ተገቢ ድጋፍ በማድረግ  ጥያቄዎቻቸውን በአግባቡ መመለስ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ በተመሳሳይ ዜና በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሁለት ዓመት አፈጻጸም ላይ የድሬደዋ ከተማ ሴቶችና ወጣቶች ተወያይተዋል። በእዚህ ወቅት ተሳታፊዎች እንደተናገሩት ለከተማ ሴቶችና ወጣቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ከተሳታፊዎቹ መካከል ወጣት አዲስ ዘመድሁን እንዳለው አምናና ዘንድሮ ለወጣቱ ብድርና ስልጠና በመስጠት ወደሥራ እንዲገባ መንግስት ያከናወናቸው ተግባራት በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥረዋል፡፡ ይሁንና የገበያ ትስስር የመፍጠር፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታዎች የማመቻቸት ክፍተቶች ቢስተካከሉ በዕቅዱ የተቀመጡ ግቦችን በተሻለ ማሳካት እንደሚቻል አመልክቷል፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚደረጉ ድጋፎች የተሻሉ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ ወይዘሮ ከዲጃ አሊ የተባሉ የድሬደዋ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ "የሴቶች ማህበራዊ፣ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማሳካት ከተፈለገ መንግስት የሚያወጣቸው ዕቅዶችና መመሪያዎች በአግባቡ ያለመተግበር ክፍተቶችን ማረም ይገባል" ብለዋል፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደርን የሁለተኛ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጻም ሪፖርት ያቀረቡት የድሬዳዋ ፕላንና ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ተሰማ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአስተዳደሩ የግብርናው ዘርፍ  በ4 ነጥብ 5 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል። በገጠርና በከተማ በመንገድ፣ በትምህርትና በጤና መስክ የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት በጥሩ አፈጻጻም ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡ የሴቶችንና የወጣቶችን ተሳተፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሥራዎች ቢሰሩም ከሚጠበቀው ግብ አንጻር በቂ ባለመሆኑ በቀጣይ የተቀናጀ ሥራ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በአስተዳደሩ የሥራ አ ጥ ምጣኔ በ2007 ከነበረበት 32 በመቶ ወደ 15 ዝቅ ቢልም ከተቀመጠው 12 በመቶ አንጻር ሲታይ ተጨማሪ ጥረቶችን ማድረግ አሰፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በውይይት መደረኮቹ ላይ የተገኙት የኢፌድሪ የመገናኛና ኢንፎርሜሽንና ቴክሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው በመላው አገሪቱ በየደረጃው ከሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር በዕቅዱ አፈጻጸም ላይ ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል። በውይይቱ ላይ ከሕብረተሰቡ የሚነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተቀምረው በቀጣይ ሁለት ዓመት ተኩል ዕቅዱን በተሻለ ለማስፈጸም ርብርብ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ አቶ ሲሳይ እንዳሉት በዕቅዱ የሁለት ዓመት ተኩል አፈጻጸም በትምህርት፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማት ዘርፎች ውጤታማ ሥራዎች ተሰርተዋል። በቀጣይ ቀሪ ዘመን ከፍተቶችን ከመድፈን ባለፈ በተለይ የግብርና ዘርፉን ምርታማነት የበለጠ በማሳደግና የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንትን ለማስፋት ርብርብ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ የሚካሄደው ውይይት በቀጣይም ከባለሃብቱና ከሲቪክ ማህበራት ጋር በተመሳሳይ ይካሄዳል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም