ቀጥታ፡

በኢንዱስትሪዎች አካባቢ የእሳት አደጋን አስቀድሞ የመከላከልና የግንዛቤ ክፍተቶች ላይ የተሰራ ጥናት ይፋ ሆነ

አዲስ አበባ  ህዳር 20/2011 በኢንዱስትሪ ፓርኮች አካባቢ  የእሳት አደጋን አስቀድሞ የመከላከልና የግንዛቤ ክፍተቶች ዙሪያ የተሰራ ጥናት ይፋ ሆነ። ጥናቱን መሰረት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለስልጣን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ በክፍለ ከተማው በኢንዱስትሪ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ባለሃብቶችንና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አወያይቷል። በክፍለ ከተማው ከሚገኙ ከ1ሺህ 500 የኢንዱስትሪ ተቋማት እንደ ናሙና ተወስደው በተመረጡት 70 የኢንዱስትሪ ተቋማት ላይ ነው ጥናቱ  የተካሄደው። በጥናቱ የተካተቱት ከተለያዩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ሲሆን ፣ ከተለያዩ የአልባሳት ማምረቻዎች፣ ከቀለም ፋብሪካዎች ፣ ከምግብ ኢንዱስትሪ፣ ከብረት ማቅለጫ፣ ከጫማ ፈብሪካና ከእንጨት ስራዎች  ይገኙበታል። በጥናቱም  ትልቁ ክፍተት በቅድመ መከላከል ላይ የግንዛቤ ማነስ ፣ በኢንዲስትሪዎች ውሰጥ ተረፈ ምርቶችን በሰዓቱና በአግባቡ አለማስወገድ፣ ምርትና ተረፈ ምርትን ለይቶ አለማስቀመጥ፣የኤሌክትሪክ ገመዶችን በጥንቃቄ አለመዘርጋት እና የመሳሰሉት እንደሆነ ተገልጿል። በተለይ  አብዛኛውን ጊዜ  በኢንዱስትሪዎች ውስጥ አለም አቀፍ የማስጠንቀቂያ ደወል አለመኖር ፣ የመቆጣጠሪያ ሰሌዳ አለመኖርና የሰራተኞችና የኢንዱስትሪ በሮች አለመመጣጠን አደጋ ሲፈጠር አባባሽ ሁኔታዎች ናቸው ተብሏል። ጥናቱ የመፍትሄ አቅጣጫ ናቸው ያላቸውን ሃሳቦች ያሰፈረ ሲሆን የኢንዱስትሪ ተቋማቱ ስራዎችን በሚያከናውኑበት ወቅት ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መሆን እንዳለበትም ያመላክታል። የኢንዱስትሪዎችን ንጽህና መጠበቅ፣ የአደጋ የመስጠንቀቂያ ምልክቶች ፣ መረጃ ሰጪ፣ በቂ የሆነ መተላለፊያ ማበጀት፣ ምርትንና ተረፈ ምርትን ለይቶ በውሉ መስቀመጥና የትኛው እሳት መጥፊያ ለየትኛው አደጋ እንደሚጠቅም ለይቶ ማወቅ በዋናነት የተቀመጡ ናቸው። በተለይ በኢንዱስትሪ ተቋማት እሳት የመነሳትና አደጋ የመፈጠር አጋጣሚ ሰፊ በመሆኑ ፣ አደጋው ከደረሰ በኋላ መልሶ ለመቋቋም አዳጋች ስለሚሆን በቅድመ መከላከልና ጥንቃቄ ላይ ሰፋ ያለ ግንዛቤ አስቀምጧል። በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ ባለሃብቶች በድርጅታቸው ፍተሻ ሊደረግ ሲል አንዳንዶች ተባባሪ አለመሆናቸው የግንዛቤ እጥረት በመሆኑ ሁሉም በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙት ለዚህ ተባባሪ በመሆን በወቅቱ የፍተሻ ስራዎችን በጋራ በመተባበር ማድረግም አንዱ መፍትሄ እንደሆነ ተቀምጧል። በዘርፉ ተሰማርተው የሚገኙ በተለይ ለቅድመ መከላከል ስራ ትኩረት በመስጠት ያሉትን ክፍተቶች በሚሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲያስተካክሉ ጥናቱ አመላክቷል። ውይይቱ በቀረበበት ወቅት የተገኙት በእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች የንፋስ ስልክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ  ወይዘሮ ቅድስት ገብረየስ እንደገለጹት፣መድረኩ የተዘጋጀው በተለይ  ኢንዱስትሪዎች የሚስተዋልባቸው የአደጋ ስጋት ሰፊ ክፍተቶችን በውይይት ለመፍታት ነው። እንደ ወይዘሮ ቅድስት ገለጻ ኢንዱስትሪዎቸ የአገሪቷ ትልቁን የልማት ኃይል የሚይዙ በመሆናቸው ፣ በክፍለ ከተማው በሚገኙት የኢንዱስትሪ ተቋማት ላይ በመዘዋወር የዳሰሳ ጥናት ከተደረገ በኋላ ነው ከባለሀብቶቹና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማትጋር ውይይቱ የተገረገው። ከመድረኩ ተሳታፊዎች የንፋስ ስልክ ቀለም ፋብሪካ የሙያ ደህንነትና የጤና አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጥበቡ ተክሌ በበኩላቸው፣እንዲህ አይነቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በተለይ እንደኛ ላሉ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች አሰፈላጊ ነው። ለግብዓትነት የምንጠቀመው በቀላሉ ተቀጣጣይ ነገሮችን በመሆኑም የእሳት አደጋ ተፈጥሮ በያውቅም የእሳት አደጋ ተነስቶ ለመቆጣጠር ተችሏል። በቀረበው የዳሰሳ ጥናትም በቅድመ መከላከል ስራዎች በእኛ ተቋም ከተጠቀሱት ውስጥ መሟላት የሚገባቸው "የቅድመ መከላከል ግብአቶች   እንዳሉ አስተውለናል ክፍተቱንም ለመሙላት ያስችለናል" ብለዋል። አብዛኛዎቹ የኢንዱስትሪ ተቋማት የቦታ ጥበትና በውስጡ ያሉትን ንብረቶች በአግባቡ አለመሰደርም ለአደጋ መፈጠር መንስኤ ነው ። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ 1ሺህ 500 የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያሉ ሲሆን በያዝነው አመትም በእነዚህ ተቋማት ላይ ምንም አይነት አደጋ እንዳልተከሰተ ወይዘሮ ቅድስት ገልጸዋል። የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚባሉት እንደ መብራት ኃይል፣ ውሃና ፍሳሽ ፣ መንገዶችና የደንብ አስከባሪዎች ሲሆኑ አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ከእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ጋር  የሚሰሩ ተቋማት በመሆናቸው በውይይቱ መሳተፋቸው ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም