ኢትዮጵያ እያደረገች ባለችው ያላሰለሰ ጥረት በቀጠናው መልካም ነገሮች እየታዩ ነው - ቲቦር ናጊ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እያደረገች ባለችው ያላሰለሰ ጥረት በቀጠናው መልካም ነገሮች እየታዩ ነው - ቲቦር ናጊ
አዲስ አበባ ህዳር 20/2011 ኢትዮጵያ እያደረገች ባለችው ያላሰለሰ ጥረት በቀጠናው መልካም ነገሮች እየታዩ መሆኑን የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል። ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ትናንት አዲስ አበባ የገቡት ቲቦር ናጊና ዶክተር ወርቅነህ በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። ረዳት ሚኒስትሩ ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት "ኢትዮጵያ እያደረገች ባለችው ከፍተኛ ጥረት በቀጠናው ላይ መልካም ነገሮች እየታዩ ነው"። በአሁኑ ሰአት በቀጠናው አገራት መካከል ያለው የንግድ ትስስርና የቀጠናው አገራት ከሌሎች አገራት ጋር ያላቸው ውጫዊ ግንኙነት እየተሻሻለ መምጣቱንና ለዚህም የኢትዮጵያ ድርሻ ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በጎረቤት አገራት ሰላም አስከባሪዎችን በመላክ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያደረገች ያለውንም ጥረት አድንቀዋል። በአሁኑ ሰአት በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አስደናቂና በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን አስመልክተው የተናገሩት ንግግር ለአፍሪካና ለተቀረው ዓለም ተምሳሌት እንደሆነ ነው ያስረዱት ረዳት ሚኒስትሩ። የአሜሪካ መንግስት ይሄን በጣም ወሳኝ ለሆነ የለውጥ እርምጃ ድጋፍ እንደምታደርግና ኢትዮጵያን እንደምታግዝም ተናግረዋል። ለውጥ ጊዜ የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ ለለውጡ ድጋፍ እንዲያደርግና ፍሬያማ እንዲሆን ትዕግስት በተሞላበት መልኩ ማገዝ አንዳለበት አሳስበዋል። በተያያዘ ዜና ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ዛሬ በተካሄደው ስድስተኛው የአሜሪካ-አፍሪካ ህብረት የከፍተኛ አመራሮች ውይይት ላይም ተሳትፈዋል። ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ጋርም ተገናኝተው መክረዋል። ረዳት ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ቀጥለው ጅቡቲ፣ ኤርትራና ኬንያ ጉብኝት እንደሚያደርጉና ጉብኝቱ በአፍሪካና በአሜሪካ መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠናከር ያለመ እንደሆነም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። የቀድሞ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ቲቦር ናጊ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከአዲሱ ሹመታቸው በኋላ የመጀመሪያቸው ነው። አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የኢኮኖሚና ዲሞክራሲ ለውጥ እንደምትደግፍና የአፍሪካ ኀብረት በአጀንዳ 2063 ያቀደውን ከግብ ለማድረስ ድጋፏን እንደምትቀጥልም ተገልጿል። ቲቦር ናጊ እ.አ.አ ከ1999 እስከ 2002 ድረስ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉ ናቸው።