የኢትዮጵያ ክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና የቡድን ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ ሆኗል

87
አዲስ አበባ ግንቦት  16/2010 በሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ የቡድን ውድድር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሸናፊ ሆኗል። ከግንቦት 13 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ እየተካሄደ ያለው ውድድር ዛሬ አራተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን በአራት ዘርፍ የቡድን ውድድሮች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ሙገር ሲሚንቶ ኢንተርፕራይዝ፣ ኦሮሚያ ፖሊስና የኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ የውድድሩ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው። በአዋቂ ወንድ፣ በአዋቂ ሴት፣ በታዳጊ ሴትና በታዳጊ ወንድ በተካሄዱ የቡድን የጠረጴዛ ቴኒስ ጨዋታዎች በአራቱም ዘርፎች የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። በቀጣይ ቀናት በሁለቱም ጾታዎች በታዳጊና አዋቂ ነጠላ፣ በጥንድ እና ድብልቅ ዘርፎች የፍጻሜ ጨዋታዎች እንደሚካሄዱ ከኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በውድድሩ ላይ በእያንዳንዱ ዘርፍ አሸናፊ ለሚሆኑ ተወዳዳሪዎች የሜዳሊያና የዋንጫ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን በአጠቃላይ የውድድሩ አሸናፊ በሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም የአፍሪካ የጠረጴዛ ቴኒስ ክለቦች ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ተገልጿል። በወጣው መርሃ ግብር መሰረት የሁለተኛው ዙር የኢትዮጵያ ክለቦች የጠረጴዛ ቴኒስ ውድድር እስከ ግንቦት 19 ቀን 2010 ዓ.ም ይቆያል። የዘንድሮው ዓመት የመጀመሪያው የክለቦች ውድድር ባለፈው ጥር ወር 2010 ዓ.ም በአፋር ክልል ተካሂዶ በአጠቃላይ ውጤት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማሸነፉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም