የቤት ባለቤት መሆናችን ለበለጠ ስራ እንድንተጋ ያነሳሳናል - በሀረሪ ክልል የቤት ተጠቃሚ መምህራን - ኢዜአ አማርኛ
የቤት ባለቤት መሆናችን ለበለጠ ስራ እንድንተጋ ያነሳሳናል - በሀረሪ ክልል የቤት ተጠቃሚ መምህራን
ሀረር ህዳር 20/2011 የቤት ባለቤት መሆናችን ለበለጠ ስራ እንድንተጋ ያነሳሳናል ሲሉ በሀረሪ ክልል የቤት ተጠቃሚ መምህራን ተናገሩ፡፡ በክልሉ የሚገኙ መምህራንን የቤት ባለቤት የማድረጉ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታውቋል፡፡ በዛሬው ዕለት በክልሉ የሚገኙ 60 መምህራንን የቤት ባለቤት ባደረገው የዕጣ አወጣጥ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ መምህራን ለኢዜአ እንደገለጹት "የቤት ባለቤት መሆናችን ለበለጠ ስራ እንድንተጋ ያነሳሳናል" ብለዋል፡፡ በሀረሪ ክልል ጀግኖች ትምህርት ቤት የሳይንስ መምህር የሆኑት ኤሊያስ አሸናፊ እንዳሉት በመምህርነት ሙያ 29 አመት ቆይተዋል፡፡ በአስተማሪነት በቆዩባቸው ጊዜያት የመኖሪያ ቤት እጦት ዋነኛ ችግራቸው መሆኑን የጠቆሙት መምህር ኤልያስ "በዛሬ ዕለት በወጣው የዕጣ ሥነ ሥርዓት ባለ ሁለት መኝታ የጋራ መኖሪያ ቤት በማግኘቴ በጣም ተደስቻለሁ" ብለዋል፡፡ የቤት ባለቤት መሆኘቸው ለበለጠ ስራ እንደሚያነሳሳቸውና የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡ የቁንድዶ ትምህርት ቤት መምህርት ዝናሽ እሸቴ በበኩላቸው ለ20 አመታት በቤት ኪራይ ሲንገላቱ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ "ይህም በስራዬ ላይ ተፅእኖ አሳድሮ ነበር" የሚሉት መምህርት ዝናሽ በአሁኑ ሰዓት ቤት በማግኘታቸው በቀጣይ ተረጋግተው መስራት እንደሚያስችላቸው አመልክተዋል፡፡ በማስተማር ስራ 34 አመት እንደሆናቸው የገለጹት መምህር ዩሱፍ ሀሰን በበኩላቸው የቤት ችግር ያለባቸውን መምህራንን በመለየት በዕጣ የቤት ባለቤት ለማድረግ የተጀመረው ስራ እሳቸውን ጨምሮ ሁሉንም መምህራንን ያስደሰተ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የቤት ችግር ያለባቸውን ከ200 በላይ መምህራን ለመለየት አምስት ቀናት መቆየታቸውን የሚናገሩት የኮሚቴው አባል መምህር ሙሉ ሃይሌ ከእነዚህም ውስጥ 60 የሚሆኑትን መምህራን በዕጣ የቤት ባለቤት ማድረግ ተችሏል፡፡ አንድ መምህር በኪራይ ቤት እየኖረ በማስተማር ስራው ውጤታማ ለመሆን አስቸጋሪ እንደሚሆንበት የጠቆሙት መምህር ሙሉ በቀጣይም የክልሉ መንግስት ቤት የሌላቸውን መምህራንን የቤት ባለቤት የማድረጉን ስራ ሊቀጥልበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራን ልማት ዳይሬክተር አቶ ጃሚዕ መሀመድ እንደገለፁት የክልሉ መንግስት መምራንን የቤት ባለቤት ለማድረግ ቅድሚያ ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ በቀጣይም የቤት ችግር ያለባቸው መምህራንን የቤት ባለቤት ለማድረግ እንዲሁም የመስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ሰነዶች እየተዘጋጁ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዮሃንስ በንቲ በበኩላቸው መምህራን ምቹና የተረጋጋ የመኖሪያ ስፍራ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ የቤት ዕድለኛ መምህራን በእውቀትና በስነምግባር የታነፀ ዜጋ ለማፍራት በሚደረገው ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊሰሩ እንደሚገባ ፕሬዝዳንቱ አሳስበዋል፡፡