ቀጥታ፡

የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፕሮግራምን ለማጠናከር የአጋር አካላት ድጋፍ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ ህዳር 20/2011 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፕሮግራምን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የአጋር አካላት የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚያሻ ተገለጸ። ፕሮግራሙን ለማጠናከር የተያዘውን ዕቅድ ለመደገፍ ኢትዮጵያና ጀርመን ዛሬ ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን የፈረሙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሒሩት ወልደማርያምና በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር ናቸው። አጋር አካላት ፕሮግራሙን በተናጠል ለመደገፍ የሚያደርጉትን ጥረት ለማደራጀት ''እሺ'' የተሰኘ የማስተዋወቂያ መርሀ ግብር ተካሂዷል። ዶክተር ሒሩት በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኢትዮጵያ በ2025 ዓ.ም ከድህነት ለመውጣት የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት የተያዘ መንገድ ሲሆን ዕቅዱን እውን ለማድረግና ለወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የተለያዩ አካላት ድጋፍ ያስፈልጋታል። እስካሁን በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት ከተቀመጠው ግብ 40 በመቶ እንኳን እንዳልተሳካ የገለጹት ሚኒስትሯ የአሰልጣኞች አቅም ማነስ፣ የግብዓት አቅርቦትና የዘርፉን ጠቀሜታ አለመገንዘብን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። በፕሮግራሙ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ወጣቶች የሰለጠኑ ሲሆን ዘርፉ ለስራ ዕድል ፈጠራ ጠቀሜታ ስላለው ለውጤታማነቱ መንግስት ከአጋር አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል። ''የዛሬው ፕሮግራም ዘርፉን የሚደግፉ አካላት በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ድጋፍ እንዲያደርጉ አንድ የድጋፍ ስርዓት መፍጠር'' ነው ብለዋል። ከጀርመን የተወሰደውን የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፕሮግራም የአገሪቱ መንግስት ሲደግፍ የቆየ ሲሆን በቀጣይም የኢትዮጵያ መንግስት የያዘውን ዕቅድ ለማገዝ የመጀመሪያውን ስምምነት አድርጓል። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በቀጣይ መድረኮችን በማዘጋጀት ዘርፉን ለማገዝ ፍላት ካላቸው አካላት ጋር ስምምነት እንደሚያደርግ ዶክተር ሒሩት ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፕሮግራምን ለማጠናከር የምታደርገውን ጥረት የአገራቸው መንግስት ከዚህ ቀደም ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። ''የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለአንድ አገር ዕድገትና ለዜጎች የስራ ዕድል ፈጠራ ወሳኝ ሚና እንዳለው የጀርመን መንግስት ያምናል'' ብለዋል። የጀርመን መንግስት ዘርፉን በስልጠና፣ በቁሳቁስ፣ በገንዘብና በሌሎችም ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆነም አምባሳደሯ ተናግረዋል። ''እሺ'' የተሰኘው መርሐ ግብር አጋር አካላት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፕሮግራሙን ለማሳደግ የተያዘውን ዕቅድ እንዲደግፉ የመግባቢያ ስምምነት እንዲፈራረሙ ማድረግ ነው። በመርሐ ግብሩ የጀርመን መንግስት የመጀመሪያውን ስምምነት ያደረገ ሲሆን በቀጣይ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚያስችል ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም