ቀጥታ፡

የታክሲ ሹፌር ረዳቶች ሳንቲማችንን አይመልሱልንም -ታክሲ ተጠቃሚዎች

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 የታክሲ ረዳቶች የሳንቲም መልሳችንን አይሰጡንም ሲሉ በአዲስ አበባ የታክሲ ትራንስፖርት ተገልጋዮች ተናገሩ። የከተማ ትራንስፖርት እድገትን የሚያፋጥኑ የንግድ፣ የኢንዱስትሪ፣ የትምህርት፣ የጤናና መሰል እንቅስቃሴዎችን በተሳካ ሁኔታ ለመደገፍ የሚያግዝ  እንደ አንድ ብርቱ ክንድ የሚታይ ዘርፍ ነው። አዲስ አበባ ከፈጣን እድገቷ፣ ከሚጨምረው ሕዝቧ፣ እንዲሁም ከቦታ ቦታ በፍጥነት ተንቀሳቅሰው ከመስራት ፍላጎት ጋር የሚሄድ የትራንስፖርት ዘርፍ ያስፈልጋታል። የትራንስፖርት ሚኒስቴር እ.አ.አ በ2011 ባደረገው ጥናት በሀገሪቷ ከሚገኙት ተሽከርካሪዎች ውስጥ 70 በመቶ ያሕሉ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ ትራንስፖርት ዘርፍ ላይ በርካታ ቅሬታዎች የሚነሳና በተለይም በስራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የስምሪት ችግር የሚታይበት ቢሆንም ለከተማዋ ትራንስፖርት አሁንም ትልቅ ድርሻ እንዳለው የሚዘነጋ አይደለም። በመዲናዋ የታክሲ ትራንስፖርት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይታወቅ እንጂ፣ የታክሲ ተጠቃሚዎች "ረዳትና ሾፌር ካልተጠየቁና ካልተጨቃጨቋቸው 25 እና 50 ሳንቲም መልስ አይሰጡም" የሚል ቅሬታቸውን ለኢዜአ ያሰማሉ። ታክሲ በምጠቀምበት "አጋጣሚ አራዳ መልስ አይጠይቅም" በሚል ታክሲ ውስጥ ተጽፎ ያየሁትን ጥቅስ አስታውሼ  እውነት ተሳፋሪዎች መልስ እንዳይጠይቁ ማስጠንቀቂያ ነው ወይ? በማለት ረዳቶችና ሾፌሮችን ጠየቅሁ። "የለም፤ እንደሱም አይደል፤ ተሳፋሪዎች የትራንስፖርት ሳንቲም ዘርዝረው አዘጋጅተው አይመጡም፤ 25 እና 50 ሳንቲሞችም በስፋት አይገኙም፤ ሳንቲም ዘርዛሪዎችም ቢሆኑ እንደልብ የሚገኙ አይደሉም" ሲሉ ረዳቶችና ሹፌሮች መልስ ይሰጣሉ። ታክሲ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች የስራው ባሕሪ ብዙ መነጋገርና በቃላት መተላለፍ የሚጋብዝ ሆኖ እንጂ እኛ መጨቃጨቅ ፈልገንና ወደን አይደለም ይላሉ። እነሱ እንደሚሉት አገልግሎት ሰጪ  ሹፌር ዝርዝር ሳንቲም ማሟላት ቢገባውም እንኳን ታክሲ ተሳፋሪዎችም ዝርዝር ይዘው መምጣት እንዳለባቸው መዘንጋታቸው  ጉዳዩ በሁለቱ ወገኖች መካከል ንትርክ እንዲፈጠር ያደርገዋል ይላሉ። በመሆኑም ረዳቶችና ታክሲ አሽከርካሪዎች ከተሳፋሪ ጋር ለንትርክ የሚጋብዛቸው "የዝርዝር ሳንቲም መጥፋት" ነው ሲሉ ዋና ችግር አድርገው ያስቀምጡታል። የሳንቲም ዘርዛሪዎች በተሳፋሪ መጫኛና ማውረጃ ቦታዎች እንደልብ አለመገኘት የሳንቲም እጥረት እንዲያጋጥም አድርጓል የሚሉት ሹፌሮች ፤ 25 እና 50 ሳንቲሞች በብዛት አለመገኘታቸው ስራውን ከባድ እንዳደረገው ያስረዳሉ። በአራዳ ክፍለ ከተማ  ፖሊስ መምሪያ ትራፊክ ፖሊስ ኮንስታብል  ደስታ ደሌ ችግሩ የሚፈጠረው ተሳፋሪና አሽከርካሪ ዝርዝር ሳንቲሞችን ይዘው መምጣትን መዘንጋታቸውና ልብ ባለማለታቸው ነው ይላሉ። የተባለው የ25 እና 50 ሳንቲሞች እጥረትም በባንኮችና ሱቆች ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ሳንቲሞች እንዳልጠፉ ማሳያ ነው ብለዋል። በመሆኑም ይላሉ ኮንስታብል ደስታ ደሌ፤ ሁሉም ሰው ከቤቱ ሲወጣ የትራንስፖርት ዝርዝር ሳንቲሞችን አዘጋጅቶ መምጣት ከቻለ ችግሩ አይከሰትም።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም