ቀጥታ፡

በብራዚል የሚገኙ ሁለት ኢትዮጵያዊን አትሌቶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ እየሰራ እንደሆነ ኮሚቴው ገለጸ

አዲስ አበባ ህዳር 20/2011 በብራዚል የሚገኙ ሁለት ኢትዮጵያዊን አትሌቶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ዝግጅቶች እያደረገ መሆኑ የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ገለጸ። የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ የውድድር ክፍል ኃላፊ አቶ ዮናስ ገብረማሪያም ከኢዜአ ጋር በባደረጉት ቆይታ ከሁለት ዓመት በፊት ለኦሎምፒክ ውድድር ሂደው ውጭ ሀገር የቀሩ ሁለት አትሌቶች ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነ ተናገረዋል። እ.አ.አ በ2016 በብራዚል በተካሄደው የሪዮ ፓራሊምፒክ ጨዋታ ወቅት ኢትዮጵያን ወክለው አራት ወንድና አንድ ሴት አካል ጉዳተኛ አትሌቶች በሩጫ ስፖርት መሳተፋቸው ይታወቃል። በወቅቱም በዚህ የፓራሊምፒክ ጨዋታ በ1500 ሜትር ሩጫ በአትሌት ታምሩ ከፍያለው ኢትዮጵያ አንድ የብር ሜዳሊያ ማግኘቷም የሚታወስ ነው። የብር ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት ታምሩ፣ እንደ ፈይሳ ሌሊሳ ሁሉ በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ያለውን ተቃውሞ ገልጾ ነበር። በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያን ወክሎ በመካፈል የብር ሜዳሊያ አሸናፊው አትሌት ታምሩ ከፍያለው እና በዚህ ውድድር የተካፈለው ሌላኛው አትሌት መገርሳ ታሲሳ በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ አስተዳደር በመቃወም ወደ ሀገራቸው ሳይመሰሉ መቅረታቸውም ይታወሳል። ሆኖም አትሌቶቹ የብራዚል ቆይታቸው እንዳሰቡት ባለመሆኑና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ እየመጣ ያለውን ለውጥ ተከትሎ ወደ ሀገራቸው መምጣት እንደሚፈለጉ ከወር በፊት ለጋዜጠኞች መግለጻቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ሁለቱ አትሌቶቹን ወጪያቸውን ሸፍኖ ወደ ሀገራቸው እንዲመጡ ለማድረግ እንዳሰበና የሚመጡበትን ወጪ ለመሸፈንም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን፣ የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴንና የስፖርት ኮሚሽንን ድጋፍ መጠየቃቸውን ገልጸዋል። ለአትሌቶቹ ወጪያቸውን መሸፈን ብቻ ሳይሆን ወደ ሀገራቸው ሲመጡም በወቅቱ በፓራሊምፒክ ለተሳተፉት ልዑካን አባላት መንግስት የሰጠውን ሽልማት ለእነዚህ አትሌቶችም እንዲሰጣቸው ለማድረግም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገሩ እንደሆነ  ነው የገለጹት። እነዚህ ሁኔታዎች ከተመቻቹ በኋላ አትሌቶቹ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ የሚደረግ ይሆናልም ብለዋል። አትሌቶቹ ወደ ሀገራቸው ከገቡ በኋላም እንደማንኛውም ሌሎች ኢትዮጵያዊን አትሌቶች ጥሩ አቅም ካለቸው በቀጣይ በሚደረጉ ውድድሮች ሀገራቸውን ወክለው የመወዳደር እድላቸው የተጠበቀ ይሆናል ብለዋል። ከፓራሊምፒክ ውድድር የተወሰነ ጊዜ ቀደም ብሎ በተካሄደው በዚሁ የ2016 የሪዮ ኦሎምፒክ ውድድር በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሁኔታ ተቃውሞ ያሰማው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ  ባለፈው ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ጨምሮ ሌሎች አመራሮችና ግለሰቦች በተገኙበት አቀባበል እንደተደረገለት ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም