የተመቻቸልን የትምህርት እድል ቤተሰባዊ ትስስራችንን አሳድጎታል...በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች - ኢዜአ አማርኛ
የተመቻቸልን የትምህርት እድል ቤተሰባዊ ትስስራችንን አሳድጎታል...በኢትዮጵያ የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች
ሽሬ እንዳስላሴ ህዳር 20/3/2011 በኢትዮጵያ በተመቻቸላቸው የትምህርት እድል መጠቀማቸው ከህዝቡ ጋር ቤተሰባዊ ትስስር እንዲያዳብሩ እያደረጋቸው መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው ኤርትራዊያን ስደተኞችና ቤተሰቦቻቸው ገለጹ። በተያዘው የትምህርት ዘመን 14 ሺህ የሚደርሱ ስደተኛ ኤርትራውያን ተማሪዎች በትግራይ ክልል በሚገኙ ትምህርት ቤቶች መደበኛ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ነው። በትግራይ ክልል በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እየተማሩ የሚገኙ ኤርትራውያን ተማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት ከኢትዮጵያውያን ጋር በአንድ ክፍል ትምህርታቸውን መከታተል መቻላቸው ቤተሰባዊ ትስስር እንዲፈጥሩ አስችሏል፡፡ በማይ ዓይኒ መጠለያ ጣቢያ ነዋሪና የአሥረኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ተስፋልደት መሃሪ እንደተናገረው ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ከኢትዮጵያውያን እህትና ወንድሞቹ ጋር በጥሩ ሁኔታ ትምህርቱን በመከታተል ላይ መሆኑን ገልጿል። “ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለቱም ለኔ እኩል መኖሪያ ቤቴ አድርጌ አስባቸዋለሁ“ የሚለው ተማሪ ተስፋልደት ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በተማረበት ሞያ በኤርትራ አልያም በኢትዮጵያ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው አስረድቷል፡፡ “ቤተሰባዊ ስሜት ተሰምቶኝ ትምህርቴን በጥሩ ሁኔታ በመከታተል ላይ ነኝ” ያለው ተማሪ ተስፋልደት መሃሪ የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት እንደሌለበትም ተናግሯል። ከኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ጋር በፍቅርና በደስታ መደበኛ ትምህርቱን በመከታተሉ ልዩ ስሜት እንደሚፈጥርበት የገለጸው ደግሞ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ክብሮም ተስፋገርግስ ነው። "ምንም እንኳ ኤርትራዊ ብሆንም ወላጅ አባቴ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ያለው በመሆኑ ወደ አባቴ ቤት እንደመጣሁ ተሰምቶኛል" ሲል ተማሪ ክብሮም አስረድቷል፡፡ ትምህርታቸውን በትግራይ ክልል እየተከታተሉ የሚገኙ ኤርትራዊያን የኢትዮጵያ መንግስት ምቹ በሆነ መልኩ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በማድረጉ እንደሚያመሰግኑ ተናግረዋል። ወይዘሮ ሮማን ክህሽን የተባሉ ኤርትራዊት አንድ ልጃቸውን በአንደኛ ደረጃ ሁለተኛ ልጃቸውን ደግሞ በቅድመ-መደበኛ ትምህርት ቤት እያስተማሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ስር የሰደደና በደም የተሳሰረና ቤተሰባዊ መሆኑን ገልጸው የተደረሰው የሰላም ስምምነት በህዝቦች መካከል ያለውን ትስስር ወደ ላቀ ደረጃ ያደርሰዋል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል። በኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳድር የሰሜን ኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የትምህርት ዘርፍ አስተባበሪ አቶ ኤፍሬም ሃጎስ እንደገለፁት ዘንድሮ 13 ሺህ 410 ኤርትራውያን በትግራይ ክልል ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። ትግራይ ውስጥ በሚገኙ ሺመልባ፣ማይ ዓይኒ፣አዲ ሃሩሽና ህፃፅ በተባሉ መጠለያ ካምፖች ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ከሚገኙ ኤርትራውያን ተማሪዎች መካከል 9 ሺህ 779 ተማሪዎች በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ናቸው፡፡ አንድ ሺህ 432 ተማሪዎች ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ኤፍሬም ሁለት ሺህ 170 ህፃናት በቅድመ-መደበኛ መርሃ-ግብር እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስረድተዋል። በአራቱ መጠለያ ካምፖች ከ200 ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች እንደሚገኙ ከዞኑ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።