ቀጥታ፡

በ4ኛው የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር ላይ የዲሲፒሊን ችግር ባሳዩ ተጫዋቾችና ክልሎች ላይ ቅጣት ተላለፈ

አዲስ አበባ ህዳር 20/2011 በ4ኛው ሀገር አቀፍ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር ላይ የዲሲፒሊን ችግር ባሳዩ ተጫዋቾችና ክልሎች ላይ ቅጣት ተላለፈ። የዓለም አቀፉ የአካል ጉዳተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ ሀገር አቀፍ የዊልቸር ቅርጫት ኳስ ጨዋታ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል። ውድድሩ ዛሬ አራተኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን ትናንት በወንዶች ውድድር ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ሲጫወቱ የኦሮሚያ ቡድን ተጫዋች የዲሲፒሊን ችግር በማሳየቱ ተጫዋቹ ላይ ቅጣት ተላልፎበታል። የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አብዱልፈታ ተማም ለኢዜአ እንደተናገሩት የኦሮሚያ ክልል ተጫዋች የሆነው ዘላለም ተመስገን የተቃራኒ ተጫዋችን በመሳደቡና ለመማታት በመጋበዙ የአንድ ጨዋታ ቅጣት ተላልፎበታል። በዛሬው እለት ደግሞ በወንዶቹ ውድድር ድሬድዋ ከተማ ከኦሮሚያ ክልልጋር ባደረጉት ጨዋታ የድሬድዋ ከተማ አንድ ተጫዋች ከተገቢው የአካል ጉዳት መጠን በላይ አሰልፎ በመገኘቱ ቅጣት ተላለፎበታል ብለዋል። ድሬድዋ ከተማ ተገቢነት የሌለው ተጫዋች አሰልፎ ኦሮሚያን 12 ለ 10 በሆነ ውጤት ነበር ማሸነፍ የቻለው። ይሁን እንጂ ድሬድዋ ከተማ  ተገቢነት የሌለው ተጫዋች አሰልፎ ያጫወተበት ደቂቃ ያህል እንደገና ተደግሞ እንዲካሄድ ሲደረግ ኦሮሚያ 13 ለ 12 በሆነ ውጤት ድሬድዋን አሸንፏል። 4ኛው የኢትዮጵያ ዊልቸር ቅርጫት ኳስ ውድድር ካለፈው ሰኞ  ጀምሮ በአዲስ አበባ ትንሿ ስታዴየም እየተደረገ ሲሆን እስከ ህዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ይሆናል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም