ቀጥታ፡

መግባባት የተሳናቸው ሁለት አገራዊ የአሰሪዎች ኮንፌዴሬሽኖች በአንድ ቀን ተመሰረቱ

አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 በትናንትናው ዕለት “የኢትዮጵያ አሠሪዎች ኮንፌዴሬሽን'’ በሚል ስያሜ በአዲስ አበባ የተመሰረቱ ሁለት አገራዊ ኮንፌዴሬሽኖች በመነታረክ ላይ ናቸው። ትናንት ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም የሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጭ አሰሪዎች፣ የኢትዮጵያ ከተሞች ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አሰሪዎች፣ የአማራ ክልል አሰሪዎች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሰሪዎች፣ እንዲሁም ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አሰሪዎች ፌዴሬሽኖች አንድ ኮንፌደሬሽን በይፋ መስርተዋል። 65ኛ የምስረታ በዓሉን ዛሬ እያከበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን በበኩሉ በተመሳሳይ ቀን የአሰሪ ኮንፌዴሬሽን መመስረቱን አስታውቋል። በኢትዮጵያ ስድስት የአሰሪ ፌዴሬሽኖች ብቻ እንደነበሩ የሚገልጹት የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች አሰሪዎች ፌዴሬሽን ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ኃይሌ ከላይ የተጠቀሱት አምስቱ ፌዴሬሽኖች በጋራ በመሆን ኮንፌዴሬሽን መመስረታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል። ኮንፌዴሬሽኑን ለመመስረት ራሳቸው የሚመሩት አደራጅ ምክር ቤት ተቋቁሞ ባለፉት አስር ወራት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ በፌዴሬሽን ደረጃ ቀደምትነት ያለው የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽንም ከመስከረም ወር ጀምሮ አደራጅ ምክር ቤቱ በተደጋጋሚ ለድርጅት ምስረታው መጠየቁን ያብራራሉ። ይሁንና ፌዴሬሽኑ ፈቃደኝነቱን የገለጸበት ጊዜ እንደነበረ ገልጸው፤ በተለይም ከ15 ቀናት በፊት በተጻፈ ደብዳቤ ለኮንፌዴሬሽኑ ምስረታ መስማማታቸውንና ተወካዮችን እንደሚልክ መግለጹን ተናግረዋል። በመጨረሻ ግን ተወካይ ከመላክም ሆነ ምላሽ ከመስጠት መቆጠቡን ተናግረዋል። “በኮንፌዴሬሽን ምስረታ ደንብ ሁለትና ከዛ በላይ የሆኑ ፌዴሬሽኖች ኮንፌደሬሽን መመስረት ይችላሉ'’ ያሉት አቶ ጌታቸው፤ በዚህም ትናንት በተካሄደ ጠቅላላ ጉባኤ አምስት አሰሪ ፌዴሬሽኖች አንድ ኮንፌዴሬሽን መመስረታቸውን አብራርተዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ታደለ ይመር በርካታ አገር አቀፍ የአሰሪ ማህበራትን ያቀፉ የአሰሪ ማህበራት እንደ ፌዴሬሽን እንደሚቆጠሩ ይናገራሉ። በዚህም ከ100 ሺህ አባላት በላይ ያላቸው በርካታ ማኅበራትና ፌዴሬሽኖች በመጣመር ከሰሞኑ ኮንፌደሬሽን መመስረታቸውን ገልጸዋል። ለአብነትም “አገር አቀፍ ደረጃ በሆቴልና መሰል አገልግሎት፣ በጤና ተቋማት፣ የነጋዴ ሴቶችንና ሌሎች አምስት አገር አቀፍ ማኅበራትና ዘጠኝ የክልል ፌዴሬሽኖችን በማካተት ነው ኮንፌዴሬሽን ያዋቀርነው'’ ብለዋል። አቶ ጌታቸው በበኩላቸው በአገሪቱ ከስድስት ፌዴሬሽኖች ውጭ እንደሌለ ገልጸው፤ በክልል ያሉትም የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን ቅርንጫፎች እንጂ ራሳቸውን ችለው የተዋቀሩና ዕውቅና የተሰጣቸው እንዳልሆኑ ተናግረዋል። ኮንፌዴሬሽን ለመመስረት የግድ ሁለት ፌዴሬሽኖች መኖር እንዳለባቸው ገልጸው፤ በፌዴሬሽን ደረጃ ያልተዋቀሩ ማኅበራትንና ሕጋዊ ሰውነት የሌላቸውን ፌዴሬሽኖች ሰብስቦ ኮንፌደሬሽን መመስረት አግባብነት እንደሌለው አስረድተዋል። “በአሰሪና ሰራተኛ አደረጃጀት ህገ ደንብ በማኅበራት ለመደራጀት ቅድመ ፈቃድ አይጠየቅም'’ የሚሉት አቶ ታደለ በበኩላቸው፤ እንዲያውም በዓለም አቀፉ የአሰሪና ሰራተኛ ስምምነት አንድ አይነት የሆነ ወይም ተመሳሳይ የሆነ ስም መጠቀም እንደሌለበት ድንጋጌውን ያብራራሉ። በዚህም መሰረት አንድ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን እያለ ሌላ የኢትዮጵያ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን መመስረት እንደሌለበት ተናግረዋል። በሌሎች ፌዴሬሽኖች ጥምረት የተመሰረተው ኮንፌዴሬሽንም አባል ለመሆን ለሚመጡ ማኅበራት የሚያሳስት ስም እንደሆነ ገልጸው፤ "ለአባልነት እስከ መማጸን ጠይቀናል መባሉ ከዕውነት የራቀ ነው" ብለዋል። ከስምንት ቀን በፊት ግን የአባልነት ጥያቄ መቅረቡን አሳታውሰው፤ "እኛ የምስረታ በዓላችንን ልናከብር ነው፤ እኛም ልንደራጅ ነው አብረን እንደራጅ" የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ይናገራሉ። “ፊት ለፊት ተገናኝተን ስላልተወያየን ላለመግባባት ችግሮች የለብንም'’ ያሉት አቶ ታደለ፤ “አሁንም ትዕግስተኛ ነን፤ አሁንም አልመሸም ወደ አንድ እንምጣ ከተባለ ዝግጁ ነን'’ ይላሉ። በአገሪቱ ሁለት ኮንፌዴሬሽኖች መመስረታቸው ችግር እንደሌለው የሚገልጹት አቶ ጌታቸው በበኩላቸው፤ "ወደ አንድ ኮንፌደሬሽን ለመምጣት በኛ በኩል ምንም ቅድመ ሁኔታ አንጠይቅም" ብለዋል። ከዚህ በፊትም ለምንመሰርተው ኮንፌዴሬሽን አጋር እንዲሆኑም ከመስከረም 2010 ዓ.ም ጀምሮ የጠየቁበት ደብዳቤ እንዳላቸው ገልጸው፤ በኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን በኩል የተቋቋመው ኮንፌዴሬሽን የእነርሱን ምስረታ ተከትሎ እንደሆነ ይናገራሉ። አቶ ታደለ ግን " እነሱን ተከትለን አይደለም፤ እኛ 2007 ዓ.ም ጀምሮ ነው ለመመስረት ያቀድነው" በማለት ጉዳዩ ከዚህ ጋር እንደማይያያዝ ተናግረዋል። ሁለቱም ወገኖች ወደ አንድ ለመምጣት ፈቃደኛ እንደሆኑ ቢገልጹም፤ እስካሁን የመጡበት መንገድ ሁለቱም ትክክለኛ እንደሆኑ በማመን መነታረካቸውን ቀጥለዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም