የአዲስ አበባ ወጣቶች ሀዋሳ ከተማ ገቡ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ወጣቶች ሀዋሳ ከተማ ገቡ

ሀዋሳ ህዳር 19/2011 ወጣቶች ኢትዮጵዊ አንድትን በማጠናከር ሀገራዊ ለውጡን ለማገዝ የሚያስችሉ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጥሪ አቀረቡ። ዛሬ ሃዋሳ የገቡ 370 የሚደርሱ የአዲስ አበባ ወጣቶች ሀዋሳ ከተማ ሲገቡ አቀባበል ተደረገላቸው በአቀባበሉ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው ለወጣቶቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በከተማዋ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታም ከሃዋሳ ከተማ ወጣቶች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉና የተለያዩ ልምዶችን እንደሚለዋወጡ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በሃዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጉብኝት እንደሚያደርጉና ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወጣቶች ጋር እንደሚወያዩም ገልጸዋል፡፡ ሰላማዊ በሆነችው ሃዋሳ ከተማ እንደልባቸው እንዲንቀሳቀሱ በመጋበዝ የሁለቱ ከተማ ወጣቶች በሚኖራቸው የጋራ ጊዜ ሃገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶችን እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ልኡካን ቡድን መሪ ወጣት ምንያህል ጌታቸው በበኩሉ ጉዟቸው ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማጠናከር ሃገራዊ ለውጡን ማስቀጠል እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ከሃዋሳ ወጣቶች በርካታ ልምዶችን እንቀስማለን የሚል እምነት እንዳላቸውም ገልጿል፡፡ ወጣቱ ከዘር፣ ከሃይማኖትና ከቀለም ነጻ በመሆን ኢትዮጵያዊነትን መስበክ እንዳለበት ተናግሯል፡፡ ወጣቶቹ ከቀናት በፊት በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ በመገኘት ጣና ሃይቅን ከወረረው የእምቦጭ አረም ለማላቀቅ የድርሻቸውን ተሳትፎ ማድረጋቸው ይታወሳል።