የተሽከርካሪዎች የፍጥነት ገደብ መሳሪያ አተገባበር መመሪያ ስራ ላይ ሊውል ነው

63
አዳማ ህዳር 19/2011 የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የፍጥነት ገደብ መሳሪያ አተገባበር መመሪያ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን አስታወቀ። ባለስልጣኑ በፍጥነት ገደብ መወሰኛ መሳሪያ አተገባበርና በጥፋተኛ አሽከርካሪዎች ሪከርድ አመዘጋገብ ሥርዓት መመሪያ ላይ ለኢንሹራንስና ለመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል። በባለስልጣን የመንገድ ትራፊክ ደህንነት የብቃት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ያቆብ በላይ  እንደገለጹት ባለስልጣኑ እየጨመረ የመጣውን የትራፍክ አደጋ ለመቀነስ የፍጥነት ገደብ መወሰኛ መሳሪያ አተገባበር መመሪያ ከመጪው ጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ ያደርጋል ። በሁሉም የንግድ ተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት ገደብ መወሰኛ መሳሪያ ለመግጠም ዝግጅት ማጠናቀቁንም ገልጠዋል።  "በመመሪያው ትግበራ ሂደት ላይ  የብዙሀን መገናኛ ባለሙያዎች ሚና ከፍተኛ ነው " ያሉት ዳይሬክተሩ "ባለሙያዎቹ ስለ መመሪያውና አተገባበሩ ግልፅ ግንዛቤ ኖሯቸው ለህብረተሰቡ እንዲያሳውቁ ለማስቻል መድረኩ ተዘጋጅቷል" ብለዋል ። የአገሪቱ የመንጃ ፍቃድ አሰጣጥ ሥርዓት ለኪራይ ሰብሳቢነት የተጋለጠና ወጥነት የሌለው በመሆኑ ለተሽከርካሪ አደጋ መበራከት መንስኤ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በባለስልጣኑ የትራፊክ ደህንነት ቁጥጥርና ክትትል ባለሙያ አቶ ያሲን ተካ ናቸው። አቶ ያሲን በመድረኩ ላይ ባቀረቡት ፅሁፍ 90 በመቶ የሚሆነው የተሽከርካሪ አደጋ በፍጥነትና በአሽከርካሪ ብቃት ማነስ ምክንያት የሚከሰት መሆኑን አመልክተዋል። በተሽከርካሪ አደጋ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለፁት አቶ ያሲን አደጋውን ለመቀነስ የፍጥነት ገደብ መቆጣጠሪያ መሳሪያ በተሽከርካሪዎች ላይ መግጠም ማስፈለጉን ጠቁመዋል ። "መሳሪያው በሶፍትዌሮች ኮምፒውተሮች አማካኝነት አሽከርካሪዎች ከፍጥነት በላይ ሲጓዙ ለመቆጣጠርና ከማስጠንቀቂያ ጀምሮ የቅጣት እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል መሆኑን አቶ ያሲን አስታውቀዋል ። በምክክር መድረክ ላይ ከግልና ከመንግስት ብዙሀን መገናኛ ተቋማት፣ከእንሹራንስ ኩባንያዎችና ከትራንስፖርት ዘርፍ የተወጣጡ ባለደርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም