የተቋማት የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ስርዓት በዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሰረት እንደሚሆን ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የተቋማት የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ስርዓት በዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሰረት እንደሚሆን ተገለጸ
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 በአገሪቱ የሚገኙ የመንግስትና የግል ተቋማት ከሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ ም ጀምሮ የፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ዓለም አቀፍ መስፈርትን ባሟላ መልኩ እንደሚሆን የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አስታወቀ። አሰራሩ ተግባራዊ በሚደረግበት ዙሪያ በኢትዮጵያ ለሚገኙ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ አካላት ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል። የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጋሼ የማነ እንደገለጹት፤ በአገሪቱ የሂሳብ አያያዝ፣ ኦዲትና ሪፖርት አቀራረብ ላይ ክፈተቶች ይስተዋላሉ። ችግሩን ለማስተካከል በኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 847/2006 የፋይናንስ ሪፖርት አዘገጃጀትና አቀራረብ አለም አቀፍ መስፈርቱን ያሟላ መሆን እንደሚገባ ድንጋጌ መውጣቱን አስታውሰዋል። 'ይሁን እንጅ አዋጁና መመሪያው ቢወጣም በአገሪቱ የሚገኙ ተቋማት የፋይናንስ አተገባባር ስርዓቱን ወጥ በሆነ መንገድ እየተገበሩ አይገኙም' ብለዋል። ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርግ የግልና የመንግስት ተቋም ተግባራዊ ሊያደርጋቸው የሚገቡ ደረጃዎችን አስቀምጦ ከሚቀጥለው ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓም ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ እንደሚጀምር ተናግረዋል። የአገሪቱ የሂሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ወጥነት የሌለውና ዓለም አቀፍ መስፈርቱን የማያሟል እንደነበር ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። የተዘበራረቀውን የፋይናንስ ሪፖርት ለማስቀረትና ዓለም አቀፍ የሂሳብ ሪፖርት አቀራረብ ስርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ የወጣው አዋጅ ከዘንድሮ የበጀት ዓመት መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልጸዋል። እዳቸው ከ100 ቢሊዮን ብር በላይና አጠቃላይ የሃብት መጠናቸው ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ተቋማት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሪፖርታቸውን ዓለም አቀፍ መስፈርቱ በሚጠይቀው መሰረት የሚያቀርቡ ይሆናል ብለዋል። እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በመካከለኛና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሌሎች ተቋማት እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 መጨረሻ ድረስ ወደ ስርዓቱ እንዲገቡ የጊዜ ገደብ እንደተቀመጠላቸው ገልጸዋል። እነዚህ ደረጃዎች ተግባራዊ መደረግ ሲጀምሩ ታክስና ግብርን በትክክል ለመሰብሰብ፣ ቁጥጥር ለማድረግና የውጭ አገሮች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። እነዚህን ደረጃዎች በደንብ ለመረዳትና የመተግበር አቅምን ለማሳደግ ለተቆጣጠሪ ተቋማት ግንዛቤ እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል። ተቆጣጣሪ ተቋማቱ ከስራቸው የሚገኙ ተቋማትን የሚቆጣጠሩ ሲሆን የኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ አሰራሩ ስለመተግበሩ ክትትል ያደርጋል ብለዋል። በኢትዮጰያ ዓለም ዓቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት ስርዓት ድጋፍ ያደረገው የዓለም ባንክ አማካሪ ማይክል ዌልዝ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እድገት እያሳየች እንደምትገኝ ገልጸዋል። የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሂሳብ አያያዝ፤ አሰራርና የሪፖርት አቀራረብ ስርዓትን ዘመናዊና በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ለማድረግ ድጋፎችን እያደረገ ስለመሆኑም ጠቁመዋል። በዋናነትም ከተለያዩ ተቆጣጣሪ አካላት ለተወጣጡ ባለሙያዎቸ ስለ ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ ዙሪያ ግንዛቤዎችን እየፈጠሩ መሆኑን የገለጹት አማካሪው ድጋፉ ተጠናከሮ የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል።