207 ኢትዮጵያዊያን ከየመን ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
207 ኢትዮጵያዊያን ከየመን ተመለሱ
አዲስ አበባ ህዳር 19/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጦርነት ውስጥ ባለችው የመን ደህንነታቸው ለአደጋ ተጋልጦ የነበሩ ዜጎች ወደ አገር ቤት እንዲመለሱ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመግባት ሲጓዙ በየመን ታስረው ከነበሩት ኢትዮጵያዊያን 207ቱ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። ሚኒስቴሩ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ተቋም (አይ.ኦ.ኤም) እንዲሁም ከኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ጋር በመሆን ዜጎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉም ታውቋል። ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን ህጋዊ ባልሆነ መልኩ የመንን በማቋረጥ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሲጓዙ የነበሩና በህግ ከለላ ስር የዋሉ ኢትዮጵያዊያን እንግልት ሳይደርስባቸው ወደ አገራቸው እየገቡ እንደሚገኝም በመግለጫው ተጠቅሷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዜጎች በሰላም እንዲመለሱ ከኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ጋር በጋራ በመሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በማመቻቸት እየሰራም መሆኑም ተመልክቷል። በመጪዎቹ ቀናትም 600 የሚጠጉ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመለስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቅድመ-ዝግጅት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።