ቀጥታ፡

የዶክተር ሀሽም ቶፊቅ ባለቤት ዊዳት አህመድ ላይ የሰባት ቀን ጊዜ ቀጠሮ ተፈቀደ

አዲስ አበባ ህዳር 19/2011 በሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው የሚፈለጉት የዶክተር ሀሽም ቶፊቅ ባለቤት ዊዳት አህመድ ላይ የ7 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ፍርድ ቤት ፈቀደ። በህግ የሚፈለጉ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪን በማሸሽና የተጠርጣሪን ማስረጃ በመሰወርና በማሸሽ ወንጀል የተጠረጠሩት ወይዘሮ ዊዳት አህመድና ወንድማቸው ሰሚር አህመድ በፌዴራሉ ፈርድ ቤት 10ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል። በዚህም ፍርድ ቤቱ በወይዘሮ ዊዳት ላይ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ውድቅ በማድረግ የሰባት ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል። እንዲሁም በህግ የሚፈለጉትን ተጠርጣሪ ዶክተር ሀሽም ቶፊቅን መቀሌ ያደረሰና በአውሮፕላን በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል ሲመለስ የተያዘው ተጠርጣሪ ሰሚር አህመድ ላይ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ ፖሊስ የጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ ውድቅ በማድረግ በ30 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጣ ፍርድ ቤቱ ፈቅዷል። ወይዘሮ ዊዳት ተጠርጣሪ የሆኑት ባለቤታቸው እንዲያመልጡ መሸኘታቸውንና በፖሊስ ሲያዙም ከሁለት ሽጉጥ ጋር እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ፖሊስ አስረድቷል። በመሆኑም ወይዘሮ ውዳት ለህዳር 26 ቀን 2011 ዓ.ም ፍርድ ቤቱ ቀጠሩ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም