ቀጥታ፡

የከፍተኛ ሊግ ህዳር 22 እና 23 ቀን 2011 ዓ.ም በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል

አዲስ አበባ  ህዳር19/2011 በኢትዮጵያ የሊግ ውድድር በሁለተኛ እርከን የሚገኘው የ2011 ዓ.ም ከፍተኛ ሊግ ህዳር 22 እና 23 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች በሚደረጉ 14 ጨዋታዎች ይጀመራል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሚያወዳድራቸው ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የከፍተኛ ሊግ ውድድር እንደሆነ ይታወቃል። ህዳር 16 እና 17 ቀን 2011 ዓ.ም የከፍተኛ ሊግ ውድድር ይጀመራል ቢባልም የእግር ኳስ ክለቦች በወቅቱ ባለመመዝገባቸው የ2011 ዓ.ም ውድድር ዓመት ለአንድ ሳምንት መራዘሙ ይታወሳል። ክለቦቹ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ምዝገባውን የማያከናውኑ ከሆኑ በተገኙት ክለቦች ብቻ ውድድሩ የሚጀመር መሆኑን የሊግ ኮሚቴው ማስታወቁም ይታወቃል። በዚህም መሰረት ምዝገባውን ባከናወኑ 28 ክለቦች መካከል ውድድሩን እንደሚጀምር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። ሌሎች ዘጠኝ ክለቦች የመመዝገቢያ ክፍያ ባለመክፈልና የተጫዋቾች ውልና ቴሴራ(የተጫዋቾች መለያ መታወቂያ) ባለሟሟላታቸው እስካሁን አለመመዝገባቸው ታውቋል። የካ ክፍለ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ፣ ሻሸመኔ ከተማ፣ አውስኮድ፣ ካፋ ቡና፣ ጅማ አባ ቡና፣ ከምባታ ሺንሺቾና አርባምንጭ ከተማ ያልተመዘገቡት ክለቦች ናቸው።   ያልተመዘገቡት ክለቦች አሁንም የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው ከተመዘገቡ በቀጣይ ሳምንት መርሃ ግብር እንደሚወጣላቸው ፌዴሬሽኑ ገልጿል። የከፍተኛ ሊግ በ2011 ዓ.ም የውድድሩን ፎርማት ከሁለት ምድብ ወደ ሶስት ምድብ በመለወጥ ይካሄዳል። በክለቦች የምዝገባ ክፍያ መዘግየት ምክንያት የከፍተኛ ሊጉ ውድድር አምናም በተመሳሳይ በተቆራረጠ ሁኔታ ዘግይቶ እንደተጀመረ ይታወሳል። የ2011 ዓ.ም አንደኛ ሊግ (ብሔራዊ ሊግ) በተመሳሳይ ችግር ውድድሩ ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙም ተገልጿል። የከፍተኛ ሊግና አንደኛ ሊግ (ብሔራዊ ሊግ) ክለቦች በወቅቱ ምዝገባ ባለማካሄዳቸው ምክንያት ውድድሮች ዘግይተው ሲጀመሩ ይስተዋላል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም