ቀጥታ፡

ብሄሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በጋራ ሊጠብቁት ይገባል---የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ

መቀሌ ህዳር 18/2011 ብሄሮች፣ ብሄሮሰቦችና ህዝቦች በመስዋእትነት ያረጋገጡትን ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ሊጠብቁት እንደሚገባ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ገለጹ። ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ወይዘሮ የምስራች ብርሃኑ የዘንድሮውን የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ምክንያት በማድረግ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት በክልል ደረጃ ዕለቱን በድምቀት ለማክበር ዝግጅት ተጀምሯል። የዘንድሮ በዓል ሲከበር የሀገራችን ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች በመስዋእትነታቸው አጽድቀውት ተግባራዊ ያደረጉትን ህገ-መንግስት ከአደጋ ለመታደግ በንቃት መጠበቅ አለባቸው። ዘንድሮ የሚከበረው በዓል ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ በወደቀበት ወቅት በመሆኑ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በጋራ ዘብ ሊቆሙ እንደሚገባም ተናግረዋል። ላለፉት አመታት በዓሉ ሲከበር በሀገራችን የተጀመሩ የልማት ስራዎች ወደ ፊት በማስቀጠል ረገድ የጎላ ድርሻ እንደነበረው የገለጹት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፣ በህዝቦች መካከል መፈቃቀርና አንድነት እንዲጎለብትም የበኩሉን ሚና መጫወቱን አስረድተዋል። በየዓመቱ በዓሉ ሲከበር በሀገራችን ያሉት ብሄሮችና ብሄረሰቦችን እኩልነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥና ህገ-መንግስታዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩ የጋራ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት መሆኑንም ተናግረዋል። በዓሉ በትግራይ ክልል በህዝባዊ ውይይቶችና በህዝባዊ ሰልፍ የሚከበር ከመሆኑም በተጨማሪ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው በዓልም የክልሉን ህዝብ ባህል በሚያንፀባርቅ መልኩ ለማክበር የልኡካን ቡድን አባላትን ማዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም