ቀጥታ፡

የጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ሁሉም ሊሰራ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ ህዳር 18/2011 ህብረተሰቡ የጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ በጤናና ኢኮኖሚ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከል መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ። የዓለም አቀፍ የጸረ-ተህዋስያን ቀንን አስመልክቶ የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። "የጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶች ከጀርሞች ጋር መላመድ ለሰው፣ ለእንስሳትና አካባቢ ጤናና ለኢኮኖሚ ከፍተኛ ስጋት ስለሆነ በተግባር የተደገፈ የባህሪ ለውጥ በማምጣት ስጋቱን ለመቀነስ" በሚል መሪ ቃል ከኅዳር 18 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ይከበራል። በዚሁ ወቅት ህብረተሰቡ በዚህ  የሚመጣውን ጉዳት ለመከላከል መድኃኒቶችን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበት የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ካይረዲን ረዲ የተናገሩት። መድኃኒትን የተላመዱ ተህዋስያን በጤና፣ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ላይ የሚያደርሱትን ችግር ለማስወገድም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል ዳይሬክተሩ። ይህን እውን ለማድረግም ህብረተሰቡ መድኃኒትን ሲጠቀም በህክምና ባለሙያ በታዘዘው መሰረት ብቻ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ በዓመት 100 ሺህ ሰዎች በዚህ ሰበብ ይሞታሉ፣ በአገሪቷ አጠቃላይ ኢኮኖሚ(GDP) ላይም የ5 ነጥብ 6 በመቶ ጉዳት ያስከትላል። በመሆኑም ህብረተሰቡ የባህሪ ለውጥ በማምጣት ጸረ-ተህዋስያን መድኃኒቶችን ከመወሰዱ በፊት አግባብ ያለው የጤና ባለሙያ ማማከርና ከታዘዘም የጤና ባለሙያው ባዘዘው መሰረት ብቻ መጠቀም እንዳለበት አሳስበዋል። ህገወጥ መድኃኒቶችን አለመጠቀም፣ መድኃኒትን ከሌሎች ሰዎች ጋር አለማጋራት እንዲሁም የአካባቢንና የግል ንጽህናን በመጠበቅ የሚደርሰውን ጉዳት ማስቀረት እንደሚያስችልም ገልጸዋል። የጤና ባለሙያዎችም ሰዎች መድኃኒት ሲገዙ በአግባቡ ስለ አጠቃቀሙ ግንዛቤ መስጠት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። መገናኛ ብዙሃንም ህብረተሰቡን ስለ ጸረ-ተህዋሲያን መድኃኒቶች በስፋት በማሳወቁ ላይ መስራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል። ጸረ-ተህዋስያንን የተላመደ በሽታ ከእንስሳትም ወደ ሰው ሊተላለፉ ስለሚችሉ የእንስሳትን ጤና በአግባቡ መጠበቅ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የእንስሳት የመድኃኒትና መኖ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የመድኃኒት ቁጥጥር ኃላፊ ዶክተር አያት ሰይድ ናቸው። በጸረ-ተህዋስያን ላይ ያለውን የግንዛቤ ችግር ለመፍታትም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም