የተረጋጋ አገራዊ ኢንዱስትሪ ለመገንባት የሶስትዮሽ ማህበራዊ ምክክሮች ሊጠናከሩ ይገባል-ዶክተር ሙላቱ ተሾመ - ኢዜአ አማርኛ
የተረጋጋ አገራዊ ኢንዱስትሪ ለመገንባት የሶስትዮሽ ማህበራዊ ምክክሮች ሊጠናከሩ ይገባል-ዶክተር ሙላቱ ተሾመ
አዲስ አበባ ግንቦት 16/2010 የተረጋጋ አገራዊ ኢንዱስትሪ ለመገንባት የአሰሪ፣ ሰራተኛና መንግስት የሶስትዮሽ ማኅበራዊ ምክክሮችን ማጠናከር እንደሚገባ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ። ዶክተር ሙላቱ ይህን ያሉት የኢትዮጵያ አሰሪዎች ፌዴሬሽን 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ሲከበር ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው። ከ65 ዓመታት በፊት በ1945 ዓ.ም የተመሰረተው 'የኢትዮጵያ አሰሪዎች ማኅበር' ፌዴሬሽኑ፤ አሰሪ ባለሀብቶችን በማደራጀት፣ አቅም በመገንባት፣ ሰላማዊ የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት በመፍጠር ለኢንዱስትሪው ምርታማነትና ለአገራዊ ዕድገት ያበረከተውን ሚና አድንቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፌዴሬሽኑ በህዳሴ ግድብ፣ በሙያ ደህንነት፣ በሴቶችና ህፃናት፣ በኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር በመከላከልና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ተሳትፎ በማድረግ ያበረከተው ድርሻ የጎላ እንደሆነ ጠቅሰዋል። 'በአገሪቱ ለሚከሰቱ ግጭቶችና አለመግባባቶች የህብረት ድርድሮችን በማካሄድ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት ይገባል' ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ፌዴሬሽኑ ለአገር ሰላምና ዴሞክራሲዊ ዕድገት ለሚያደርገው ተሳትፎ መንግስት ከጎኑ እንደሚቆም አረጋግጠዋል። በመሆኑም የተረጋጋ አገራዊ ኢንዱስትሪ ለመገንባት አሰሪው፣ ሰራተኛውና መንግስት መካከል የሚደረጉ ማኅበራዊ ምክክሮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር በበኩላቸው፤ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ለመውጣት በሚጣጣሩበት ወቅት የተመሰረተው ፌዴሬሽኑ የመደራጀት ህግ ሳይኖር ማህበር በማቋቋም፣ በሰራተኛና አሰሪዎች መካከል የህብረት ድርድር በመፍጠርና በመዳኘት ትልቅ ስኬቶች ማስመዝገቡን አውስተዋል። በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ማህበራት አባል በመሆን፣ የአፍሪካ አሰሪዎች ኮንፌዴሬሽን መስራች አባል መሆኑንም ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ የደርግ ስርዓት ሲመጣ በነበረው ርዕዮተዓለም የተነሳ ተሰርዞ መቆየቱን አስታውሰው፤ ስርዓቱ ከወደቀና አዳዲስ የህግ ድንጋጌዎች ከወጡ በኋላ በ1989 ዓ.ም ዳግም መመስረቱን ተናግረዋል። ዳግም ከተቋቋመ በኋላ በኢንዱስትሪ አካባቢ ቅርንጫፍ በማደራጀት፣ የተለያዩ አሰሪ ማህበራትን በማቋቋምና የአባላቱን ቁጥር በማሳደግ፣ በመንግስት የህግ ማዕቀፎች ረቂቅ ዝግጅት ላይ በመሳተፍ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። ፌዴሬሽኑ ከ30 ሺህ በላይ አባላት ያላቸው 25 አሰሪ ማህበራትን ያቀፈ መሆኑን አቶ ታደለ ገልፀው፤ በኢንዱስትሪ ሰላም፣ በምርትና ምርታማነት፣ በገበያ ተወዳዳሪነት መጎልብት ዙሪያ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል። የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ የተለያዩ አለመግባባቶችና ግጭቶች እንደሚከሰቱ ገልጸው፤ ፌዴሬሽኑ ለኢንዱስትሪ ሰላም መስፈን ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንቅስቃሴዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት። 'የተደራጀ ያሸንፋል' ያሉት አቶ ታደለ፤ 'በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ያለፈው ፌደሬሽን 65ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ባሳለፋቸው ዓመታት ያጋጠሙትን ችግሮች በመፍታት አደረጃጅቱን በማጠናከር ለበለጠ ውጤታማነት ለመትጋት በማለም ነው' ብለዋል። በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የዓለም አቀፉ የስራ ድርጅትና ሌሎች አጋር አካላት ከፌዴሬሽኑ ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ድጋፍ እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።